ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

ግንቦት 19/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ተገልጿል።

“አዲሷን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መዳረሻ ኢትዮጵያን እናስስ” በሚል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎችና የአሜሪካ ባለሃብቶች የተሳተፉበት የበይነ መረብ ውይይት ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት እየሰራች ያሉ ሥራዎችን በሚመለከታቸው ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አህመዲን መሐመድ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፣ ኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችላትን የዘርፉን ማሻሻያዎች በማድረግ የዲጂታል መሰረት እየጣለች ነው።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂና የኤሌክትሮኒክስ ትራንዛክሽን አዋጅ መፅደቁ፣ የዲጂታል መታወቂያ ወደ ትግበራ መግባት፣ የስታርት አፕና የግል መረጃ ጥበቃ አዋጅ በረቂቅ ሂደት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በተጨማሪም የመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት፣ ኢኮሜርስና የመሳሰሉት ኢትዮጵያ በልዩ ትኩረት እየሰራችባቸው ስለመሆኑ ገልጸው፤ ኢትዮጵያን “የአፍሪካ ኢኖቬሽን መዳረሻ” ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍፁም አረጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት መንግስት ምቹ የንግድ ከባቢ ሁኔታን ለመፍጠርና የውጭ ባለሃብቶችን ለመሳብ የተለያዩ የህግ ማሻሻያዎች እያደረገ ነው።

በዚህም በግሉን ዘርፍ የሚመራ ኢኮኖሚን ለመገንባትም የንግድ ህግ ማሻሻያ መደረጉንና የኢንቨስትመንት አዋጅ መውጣቱን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካሪ ሜሪያም ሰይድ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ ከመንግስት መር ኢኮኖሚ በግሉ ዘርፍ ወደሚመራ ኢኮኖሚ ሽግግር እያደረገች ነው ያሉት።

የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚው ተዋናይ እንዲሆን ለማድረግም የንግድ ስራ ቅልጥፍና ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት አማካሪዋ፣ የቴሌኮም ዘርፉን በከፊል ወደ ግል የማዞር ስራ፣ የዲጂታል ክህሎት ግንባታ፣ የመረጃ መረብ ደህንነት ጥበቃ፣ የግለሰብ የመረጃ ጥበቃ አዋጅ ለዘርፉ መደላልድል ለመፍጠር እየተሰራባቸው መሆኑን አብራርተዋል።

የአሜሪካ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የዘርፉን ማሻሻያ እንደ መልካም አጋጣሚ በመውሰድ በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ መቅረቡን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።