ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ጣሊያን ላይ በተደረጉ የአገር አቋራጭ ውድድሮች አሸነፉ

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨረሻ ጣሊያን ሳን ቪቶሬ ኦሎና ላይ በተደረጉ የአገር አቋራጭ ውድድሮች አሸንፈዋል።
በወንዶች በተካሄደው የ10 ኪ.ሜ ውድድር አትሌት ንብረት መልዓክ ውድድሩን በአንደኝነት ጨርሷል።
የአለም ሻምፒዮኑ እና ሌላኛው የአገር አቋራጭ ውድድሩ ተሳታፊ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ሶስተኛ ሆኗል።
ኬንያዊው ሌኦናርድ ቤት ደግሞ የሁለተኝነቱን ቦታ ወስዷል።
አትሌት መልዓክ ንብረት ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ ጣሊያን ኮምፓሲዮ ላይ በተከናወነው የ10 ኪ.ሜ ውድድር ዩጋንዳዊውን ጃኮብ ኪፕሊሞን በመከተል ሁለተኛ ሆኗል።
እንዲሁም በሴቶች በተደረገ የ 6.2 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር አትሌት ፀሀይ ገመቹ 1ኛ ወጥታለች።
አትሌት ጸሃይ ገመቹ ባለፈው ሳምንት በተመሳሳይ በጣሊያን ኮምፓሲዮ በተከናወነው የ6 ኪ.ሜ የሩጫ ውድድር 1ኛ መሆኗ ይታወሳል።
በሳን ቪቶሬ ኦሎናው የአገር አቋራጭ ውድድር የተሳተፉት አለሚቱ ታሪኩ እና አዲስ ዓለም በላይ ደግሞ እንደየቅደም ተከተላቸው 4ኛ እና 7ኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።
ኬንያውያኑ ቤትሪስ ቼቤት እና ሼላ ቼላንጋት ጸሃይ ገመቹን በመከተል ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመሆን መግባታቸውን ከአፍሪካን አትሌቲክስ ዩናይትድ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡