ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ መንገድ ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሯ ተገለጸ

መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ መንገድ ዝናብ እንዲዘንብ የሚያደርግ ቴክኖሎጂ መጠቀም መጀመሯን የብሔራዊ ሜቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር ክንፈ ሃ/ማሪያም ዝናብ ከውሃነት እንደሚጀምር በማስረዳት ከውቂያኖስ እና ሌሎች መሬት ላይ ካሉ የውሃ አካላት ከፀሀይ በሚመጣ የሙቀት ሃይል ከተነኑ በኋላ በጋዝ መልክ ወደ ሰማይ እንደሚወጡ አስረድተዋል፡፡
ወደ ደመናነት የሚቀየረውን ወደ ዝናብነት ለመቀየር ውሃ የሚሰበስብ ንጥረ ነገር እንደሚያስፈልግም በማንሳትም ንጥረ ነገሩ በተፈጥሮ አየር ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡
ነገር ግን ይህ ንጥረ ነገር በቂ ሳይሆን ሲቀር ደመናን ወደ ዝናብነት ለመቀየር በሰው ሰራሽ መንገድ ደመናን በማበልፀግ ወይንም በክላውድ ሲዲንግ ቴክኖሎጂ ዝናብ ማዝነብ እንደምቻልና ኢትየጵያም ይህን ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯን ገልፀዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባገኘችው ድጋፍ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሯ ያነሱት ም/ዋና ዳይሬክተሩ፣ ከጣና በስተምዕራብ በምትገኘው ሻውራ አካባቢም የአየር ሁኔታ ራዳር ተተክሏል ሲሉ አክለዋል፡፡
ደመናን የማበልፀግ ቴክኖሎጂ ደረቃማ የአየር ሁኔታ በሚስተዋልባቸው ወቅቶች ተጨማሪ ዝናብን ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ቴክኖሎጂ እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
ደመናን የማበልፀግ ክላውድ ሲዲንግ ቴክኖሎጂ በተለያዩ የአለማችን አገራት ተተግብሮ ውጤታማ መሆን የቻለ ቴክኖሎጂ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በቴክኖሎጂው ከ15 እስከ 30 በመቶ ተጨማሪ ዝናብ የምታገኝ ሲሆን፣ ቻይና እስከ 55 ቢሊየን ቶን ተጨማሪ ውሃ በዚህ ቴክኖሎጂ ታገኛለች ተብሏል፡፡
(በሳሙኤል ሀጎስ)