ኢትዮጵያ እና ምርጫ

ኢትዮጵያ እና ምርጫ
ምርጫ ለአገራችን ኢትዮጵያ እንግዳ ነገር አይደለም፡ባህላዊ ምርጫ በሁሉም ማኅበረሰብ ዘንድ ከጥንት ጀምሮ የነበረ ነው፡፡ ሕዝቡ በየአካባቢው ኑሮውን፣ እምነቱንና ተስፋውን ለመጠበቅ ተሰባስቦ የመምከር፣ የሀገር ሽማግሌዎችን የመምረጥና የመሰየም የቆየ ልማድ ነበረው፤ አለውም፡፡ የሚመረጡት ሽማግሌዎች የሚከተሏቸውና የሚያከብሯቸው ባህላዊ ሕጎች አሏቸው፡፡ ሸንጎ፣ ገዳ፣ ጐርዶና ሴራ፣ ጆንዶንጐ፣ ኮሞሩ እንደቅደም ተከተላቸው በአማራ፣ በኦሮሞ፣ በጉራጌ፣ በአኝዋክና በሱርማ ሕዝቦች ዘንድ የሚታወቁ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓቶች ሲሆኑ ከበርካታ ባህላዊ ህጎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከባህላዊ የአስተዳደር ምርጫዎች በተጨማሪ እስካሁን ድረስ ዘልቀው የቆዩ የበጎ ፈቃድ ማኅበራት አሉ፡፡ ስማቸው ከቦታ ቦታ ይለያይ እንጂ አብዛኞቹ የማኅበረሰብ የእርስ በርስ መረዳጃ ተቋማት ናቸው፡፡
ብዙ ጊዜ በምሳሌነት የሚጠቀሱት እቁብ፣ እድር፣ ሰንበቴ፣ ወዘተ ናቸው፡፡ የእቁብ ዳኞች፣ የእድር መሪዎችና የሰንበቴ ሙሴዎች የሚመረጡት ከማኅበሩ አባላት ውስጥ በማኅበርተኞቹ ቀጥተኛ ተሳትፎ ነው፡፡ እነኚህ ማኅበራዊ ተግባራት የኢትዮጵያውያንን የመምረጥና የመመረጥ የቆየ ልምድ የሚያመለክቱ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ፡፡
አንድ ምርጫ በዘውዳዊ ሥርዓት (የዘውዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆየው እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ ነው፡፡) በዚህ ረዥም ዘመን በሀገራችን ውስጥ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረግ ምርጫ አይታወቅም፡፡ በዘውዳዊ ሥርዓት የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በዘር ሐረግ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በ1900ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት በዐፄ ምኒሊክ አማካይነት የሚኒስቴር አደረጃጀት ሲቋቋም ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ የተመረጡ ሰዎች በሓላፊነትና በአማካሪነት በንጉሠ ነገሥቱ አካባቢ እንዲቀመጡ ተደርጓል፡፡ በተመሳሳይ በ1911 ዓ.ም. ከየጠቅላይ ግዛቱ የተመረጡ መሳፍንትና መኳንንት (ወይንም የእነርሱ ቤተሰብ አባላት) ንጉሠ ነገሥቱን በምክር እንዲረዱ በቤተመንግሥቱ ውስጥ ልዩ ቦታ ተሰጥቷቸው ሀገራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ወደ ሕዝቡ ከመድረሱ በፊት እንዲመክሩበት ይደረግ ነበር፡፡ ይህ አሠራር እስከ 1924 ዓ.ም. ድረስ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
በ1923 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሕገ መንግሥት ተዘጋጅቶ ተግባር ላይ ሲውል በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ ሁለት ምክር ቤት ፓርላማ ተቋቋመ፡፡ ምክር ቤቶቹ የሕግ መወሰኛና የሕግ መምሪያ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ሆኖም ሕዝቡ መማክርቱን (ማለትም የምክር ቤቶቹን አባላት) የመምረጥ መብት አልነበረውም፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 32 መሠረት፤ ‘‘የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላትን ሕዝቡ ራሱ በቀጥታ መምረጥ እስከሚችል ድረስ እስከተወሰነ ዘመን ድረስ አማካሪዎቹ በመኳንንቶችና በሀገር ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡” ሕገ መንግሥቱ ይህን ቢደነግግም የምርጫው የበላይ አስተናባሪ ንጉሠ ነገሥቱ ራሳቸው ነበሩ፡፡ ይህ የምርጫ ሥርዓት በጣሊያን ወረራ ሳቢያ ተስተጓጐለ እንጂ ከ1924 እስከ 1934 ዓ.ም. ድረስ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በ1935 ዓ.ም. ምንም ዓይነት ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ሳይደረግ አዲስ አሰራር ሥራ ላይ ዋለ፡፡ በአዲሱ አሠራር መሠረት የሕግ መምሪያ ምክር ቤት አባላት በንጉሡ መመረጣቸው ቀርቶ ከየጠቅላይ ግዛቱ ወረዳዎች የተውጣጡ አምስት አምስት ተመራጮች በጠቅላይ ግዛት ደረጃ ተሰባስበው አምስት ተመራጮችን እንዲመርጡና ለምክር ቤት ውክልና ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ ይደረግ ጀመር፡፡
በዚህ መልክ ተመርጠው የተወከሉት የፓርላማ አባላት እስከ 1949 ድረስ ለ15 ዓመታት በአማካሪነት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡በ1948 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ተደረገ፡፡ በ1948ቱ ሕገ መንግስት መሰረት ሕዝቡ ተወካዮቹን (እንደራሴዎቹን) ራሱ እንዲመርጥ ተፈቀደ፡፡ መራጮች ዕድሜአቸው 21 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የኖሩና በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ተመራጮች ደግሞ ዕድሜያቸው 25 ዓመትና ከዚያ በላይ፣ በሚኖሩበት አካባቢ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የኖሩ፣ ዋጋው ከብር ሁለት ሺህ ያላነሰ ተንቀሳቃሽ ንብረት ወይንም ብር አንድ ሺህ የሚገመት የማይንቀሳቀስ ንብረት ያላቸው፣ ማንበብና መጻፍ የሚችሉ፣ እዳ የሌለባቸውና በትውልድ ኢትዮጵያዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መምረጥም ሆነ መመረጥ ለሁለቱም ፆታዎች እኩል የተፈቀደ ነበር፡፡ በዚህ አግባብ የተመረጡት የየጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴዎች እስከ የካቲት 1966 አብዮት ድረስ አገልግለዋል፡፡ በእነዚህ 18 ዓመታት ውስጥ በሀገሪቱ በየአራት ዓመቱ አምስት ምርጫዎች ተካሂደዋል፡፡ምርጫ በጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (1967 – 1979)ከ1967 እስከ 1979 ዓ.ም. ድረስ በሀገራችን ምንም ምርጫ አልተካሄደም፡፡
በ1967 የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሥልጣን ሲይዝ የዘውዳዊው ሥርዓት ሕገ መንግሥት ታግዶ፣ ፓርላማው ተበትኖ፣ አስተዳደሩ በጊዜያዊነት ተሰየመ፡፡ በጥቅምት 1967 በፓርላማው ምትክ የመማክርት ጉባዔ ተቋቋመ፡፡ የጉባዔው አባላት 60 ሲሆኑ ከተለያዩ ወታደራዊ ክፍሎችና መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ ነበሩ፡፡ የመማክርት ጉባዔ ስራ ላይ የነበረው እስከ 1978 መገባደጃ ድረስ ነበር፡፡ በ1979 ዓ.ም. የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ራሱን ወደ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢ.ሕ.ዲ.ሪ.) ቀየረ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 314/1979 አማካይነት ብሔራዊ የምርጫ ኮሚሽን ተቋቁሞ የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. መንግሥት ተመሠረተ፡፡ ምርጫ በኢሕዲሪ መንግሥት (1980 -1983) ጥር 24 ቀን 1979 ዓ.ም. የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት ጸድቆ በዓመቱ መጨረሻ ብሔራዊ ሸንጎ በመባል የሚታወቅ ምክር ቤት ተቋቋመ፡፡
ሸንጎው 835 አባላት የነበሩት ሲሆን የሥራ ዘመኑ አምስት ዓመት ነበር፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሀገሪቱ በአስተዳደር አካባቢዎችና በራስ ገዝ አካባቢዎች ተከፋፍላ ተዋቀረች፡፡ የብሔራዊ ሸንጎው አወካከል በሕዝብ ቁጥርና በብሔረሰብ ላይ የተመሰረተ ነው ቢባልም አመራረጡ ድርጅታዊ በመሆኑ ተአማኒና ሕጋዊ አልነበረም፡፡
የሸንጎው አባላት (ወይንም የሕዝብ እንደራሴዎች) ምርጫ የጥር 1979ን ሕገ መንግሥት ተከትሎ በወጣው የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ አዋጅ ቁጥር 23/1980 አማካይነት የተካሄደ ነበር፡፡ ምርጫው የሚከተሉትን አራት የምርጫ መሠረተ-ሐሳቦችን አካትቶ የያዘ ነበር፡፡ ያለምንም አድልዖና ልዩነት (የብሔረሰብ፣ የጾታ፣ የዘር፣ የቀለም፣ የሃይማኖትና የሥራ ዓይነት) ሁሉም ዜጋ በምርጫ ይሳተፋል፣በየደረጃው ለሚካሄድ የሕዝብ እንደራሴዎች ምርጫ እያንዳንዱ መራጭ አንድ ድምፅ ብቻ ይኖረዋል፤ እያንዳንዱም ድምፅ እኩል ዋጋ ይኖረዋል፣ ምርጫው ቀጥተኛ ሆኖ በግምባር በመቅረብ አንድ ጊዜ ብቻ ይከናወናል፣ ምርጫው ሚስጥራዊ የድምፅ አሰጣጥ ስርዓትን ይከተላል፡፡ ለብሔራዊ ሸንጎ የሚወዳደሩ እጩዎችና መራጮች በትውልድ ኢትዮጵያዊ፣ ከአእምሮ ሕመም ነፃ መሆናቸው የተረጋገጠና በፍርድ ቤት ውሳኔ ቅጣት በመቀበል ላይ ያልሆኑ መሆን አለባቸው፡፡
በተጨማሪም የመራጮች ዕድሜ 18 ዓመትና ከዚያ በላይ፤ የተመራጮች ዕድሜ ደግሞ 21 ዓመትና ከዚያ በላይ መሆን ይኖርበታል፡፡ መራጮች የምርጫ ጣቢያው ኗሪ መሆናቸው ብቻ የግድ ሲሆን ተመራጮች ግን በሚመረጡበት አካባቢ ቢያንስ ለአምስት ዓመታት የኖሩ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ነገር ግን የመምረጥና የመመረጥ መብት ለሁለቱም ጾታዎች እኩል ክፍት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በ1979ኙ ሕገ መንግሥት መሰረት፤ ‘‘እጩዎችን መጠቆም የሚችሉት የኢሠፓ አባላት፣ ሕዝባዊ ድርጅቶችናወታደራዊ ክፍሎች ብቻ ነበሩ፡፡ የሕዝባዊ ድርጅቶች አመራር አባሎችና የወታደራዊ ክፍሎች አመራሮች በኢሠፓ አመራር የተመሰረቱና የሚንቀሳቀሱ ስለሆኑ ዞሮ ዞሮ የእጩዎች ጥቆማ የሚደረገው በፓርቲው ብቻ ነበር፡፡” በመሆኑም የምርጫው ሂደት እንዳሳየው የኢ.ሕ.ዲ.ሪ. ምርጫ የአንድ ፓርቲ ድርጅታዊ አሠራር ተግባራዊ የሆነበት ነበር፡፡ እጩውን የሚጠቁመው የኢሠፓ አባል፣ በእጩነት የሚቀርቡት የኢሠፓ ከፍተኛ አመራሮችና አባላት፣ አስመራጩ የኢሠፓ አባል፣ ተመራጩም የኢሠፓ አባል ነበር፡፡ ይቀጥላል%
ዋቢ መጻሕፍት በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን 5ኛ ዙር አካባቢያዊ እና 6ኛ ዙር አገራዊ ምርጫ በተመለከተ የተካሄደ የሕዝብ አስተያየት ጥናት፣ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት፣ ግንቦት፣ 2011 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የተወካዮች ምክር ቤት (1987) የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ አንደኛ ዓመት፣ ቁጥር 1፣ አዲስ አበባ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ (2003) የመራጮችና የሥነዜጋ ትምህርት ማሰልጠኛ ማኑዋል፣ አዲስ አበባ፤ Cowen, Michael and Liiasa Laakso (eds.). Multi-party Election in Africa. Oxford: James Curry, 2002.National Electoral Board, Election Officers Manual, Addis Ababa, 2000.
(በተረፈ ወርቁ)