ኢትዮጵያ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ስርዓተ-ትምህርት ሊትቀርጽ እንደሚገባ ተገለጸ

                                          የከዋክብት ተመራማሪ ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ

ኢትዮጵያ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ስርዓተ-ትምህርት እንድትቀርጽ የህዋ ሳይንስ ተመራማሪዎች ጠየቁ፡፡

ህፃናት እና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የሳተላይት ቴክኖሎጂ ስልጠና በከፍተኛ ትምህርት ደረጃ ሊሰጥ እንደሚገባም የዘርፉ ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡

የከዋክብት ተመራማሪ ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ በታዳጊ ሀገራት የህዋ ጥናት አስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ቢነሳም፤ የበለፀጉ ሀገራት ህዋ ሳይንስ ለእድገታቸው ትልቅ ጠቀሜታ እንዳስገኘላቸው ገልጸው፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ሳይንሱ በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡

ኢንዱስትሪው በኢትዮጵያ እንዲያድግ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ባይሆኑም በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች የሳተላይት ቴክኖሎጂ ትምህርት ሊሰጥ እንደሚገባ የሚናገሩት የከዋክብት ተመራማሪው፣  ኢትዮጵያ የሳተላይት ቴክኖሎጂ በሚል እራሱን የቻለ ስርዓተ-ትምህርት ተቀርጾ መተግበሩ እጅግ ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የከተሞች መስፋፋት እና ኢንቨስትመንቶች እየጨመሩ ሲሄዱም በዛው መጠን የመረጃው አስፈላጊነት ከፍ ስለሚል በዘርፉ የተማረ የሰው ሀይል ማመንጨትን ግምት ውስጥ ያስገቡ ተግባራት ማከናወን እንደሚገባም የከዋክብት ተመራማሪው ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ አሳስበዋል፡፡

መንግስት አስፈላጊ ግብዓቶችን በማቅረብ በሳተላይት ቴክኖሎጂ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ኢትዮጵያ በዘርፉ ከምስራቅ አፍሪካ ተሻግራ በአፍሪካ ተጠቃሽ ሀገር ለማድረግ መስራት ይጠበቅበታልም ብለዋል፡፡

                         የአንድሮሜዳ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ መጋቢ ሀዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ

የአንድሮሜዳ ቴሌቪዥን ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ መጋቢ ሀዲስ ዶ/ር ሮዳስ ታደሰ በበኩላቸው፣ የህዋ ጥናት በዓለም ላይ በፍጥነት እየዘመኑ ካሉ ዘርፎች መካከል ግንባር ቀደም መሆኑን ገልጸው፣  ህፃናት እና ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ ስልጠና በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የህዋ ሳይንስን ለሰላማዊ ግልጋሎት መጠቀም ለእድገት እና ብልፅግና ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፤ የህዋ ሳይንስ እርሻን፣ የደን ሽፋንን፣ ውሃና ማዕድናት የሚገኝባቸውን አካባቢዎችን መለየትና መከታተል የሚያስችሉ ተግባራትን መከወን ያስችላሉም ነው የተባለው፡፡

እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቆጣጠር፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ከመድረሳቸው አስቀድሞ ለመተንበይ እና ደህንነትን ለመጠበቅ እንደሚረዳም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ዘርፍ ከበለፀጉ ሀገራት ተሞክሮ በመነሳት የህዋ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል እየሠራችበት ትገኛለች፡፡

ኢትዮጵያ በህዋ ሳይንስ ቀደምት የመጠቀ ታሪክ ቢኖራትም አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያ ከተቀረው ዓለም አንጻር ጀማሪ ስትሆን፤ አፍሪካ ውስጥ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ አልጄሪያ እና ግብጽ ጥሩ ስም ካላቸው ሀገራት መካከል ናቸው።

ኢትዮጵያ አሁን ላይ  “ህዋ ለልማት” የሚል የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ትብብር ቢሮ አቋቁማ አበረታች እንቅስቃሴ ማድረጓ ተጠቃሽ ስኬት ነውም ተብሏል።

(በደረሰ አማረ)