ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የምታከናውነው በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ነው – አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት የምታከናውነው በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሆኑን በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ገለጹ።

አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ከፍራንስ 24 የቴሌቪዝን ጣቢያ ጋር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴው ግድብ ፕሮጀክት ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል።

ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ የምትገነባው ሁሉንም የተፋሰሱ ሃገራት ባማከለ መልኩ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ መሰረት መሆኑንም ነው ያብራሩት።

“ግድቡ ለኢትዮጵያውያን የሞትና የህይወት ጉዳይ የሚያደርገው 65 ሚሊዮን የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መብራት እያገኙ ባለመሆናቸው ነው” በማለት፤ ይህ ሁኔታ ሊቀጥል የማይገባው መሆኑንም ገልጸዋል።

የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት የሚያቀርቡት ሃሳብ በተመለከተ ግድቡ የሚገነባው ኤሌክትሪክ ለማመንጨት በመሆኑ የውሃው መጠን ስለማይቀንስ ምንም አይነት ስጋት ሊፈጥር እንደማይገባም ነው የተናገሩት።

ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ግብጽንም ሱዳንንም የሚጠቅም በመሆኑ ስጋታቸው መሰረት እንደሌለው ተናግረዋል።

“ከግንዛቤ ውስጥ መግባት ያለበት ግድቡ የሚገነባው ለሃይል ማመንጫ ታስቦ በመሆኑ ውሃው መፍሰሱን አያቆምም” ያሉት አምባሳደሩ በመርህ ደረጃ ሊረሳ የማይገባው ነገር ቢኖር ሰማንያ ስድስት በመቶ የሚሆነውን ውሃ የምታመነጨው ኢትዮጵያ ህዝቧ በድህነት ውስጥ እየኖረ እንኳን አንዲት ጠብታ ውሃ አልተጠቀመችም ብለዋል ።

“ኢትዮጵያውያን መልማትና ህይወታቸውን መቀየር የሚፈልጉ በመሆኑ በሃያ አንደኛው ክፍለዘመን አንደኛው ወገን እየተጠቀመ ሌላኛው የሚጎዳበት አካሄድ ሊኖር ስለማይገባ ሁሉም ወገን ተጠቃሚ የሚሆንበት መፍትሄ መፈለጉ የግድ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያን እንደ ሱዳናውያንና ግብጻውያን ወንድሞቻቸው መልማትና መለወጥ የሚፈልጉ መሆኑን በማስታወስ፤ ታሪካዊ ኢፍትሃዊነቶች ሊስተካከሉ የሚችሉት የአፍሪካ ህብረት በሚመራው ስምምነት መሆኑንም አስምረውበታል ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።