ኢትዮጵያ የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት አቅሙና ጥበቡ አላት – የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር

ታኅሣሥ 7/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት አቅሙና ጥበቡ ያላት ሀገር መሆኗን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ከስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄነሪስ ሉንዱኪስት ጋር በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢኖቬሽንና በሌሎች ወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መክረዋል።

ስዊድን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ የዳበረ ልምድ ያላት ሀገር በመሆኗ ኢትዮጵያ ይህንን ልምድ መውሰድ እንደምትፈልግና ድጋፍም እንደምትሻ ሚኒስትሩ ገልፀዋል።

ስዊድን በተለያዩ መስኮች ለኢትዮጵያ በምታደርገው ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት ሚኒስትሩ በአይ ሲ ቲ እና ዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ኢትዮጵያ ያለባትን የሰው ኃይል ክፍተት ለመሙላት ስዊድን ቀደም ሲል ስታደርግ የነበረውን ትብብርና ድጋፍ አጠናክራ እንድትቀጥልም ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሀንስ ሄነሪስ ሉንዱኪስት በበኩላቸው በቴክኖሎጂና ስራ ፈጠራ፣ በትምህርትና ግብርና ዘርፍ ኢትዮጵያን ለመደገፍ ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗን ማረጋገጣቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ከ13 በላይ የስዊድን ካንፓኒዎች እንዳሉ የገለፁት አምባሳደሩ አሁን ባለው ሀገራዊ ሁኔታ በስዊድን በኩል ያለውን ስጋት ያነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ አሁን የገጠማትን ውስጣዊ ችግር ለመፍታት አቅሙና ጥበቡ ያላት ሀገር መሆኗን ሚኒስትሩ ለአምባሳደሩ አረጋግጠውላቸዋል።