ኢንስቲትዩቱ ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ እንዲያውል ተጠየቀ

የኢትዮጵያ ስፔስ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ከሳተላይት የሚገኙ መረጃዎችን በአግባቡ ሥራ ላይ ማዋል እንዳለበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ፡፡

በምክር ቤቱ የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንስቲትዩቱን የሥራ እንቅስቃሴ ለመገምገም የመስክ ምልከታ አካሄዷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ከሳተላይት የሚገኙ በተለይም ተደክሞባቸው ለሀገር ፋይዳ ያላቸው  መረጃዎች አጥጋቢ  የግንዛቤ  ሥራ ባለመሰራቱ ምክንያት ወደ ተጨባጭ ተግባር እየተቀየሩ አለመሆናቸውን የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ እምዬ ቢተው ተናግረዋል፡፡

የስፔንስ፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ለሀገር ያለውን ፋይዳ በተመለከተ ለማሕበረሰቡ ከማስተዋወቅ አንጻርም ኢንስቲትዩቱ ክፍተት እንዳለበት ጭምር አንስተዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱን ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች አቅም ለመገንባት እና ጥቅም ለማስጠበቅ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባም ቋሚ  ኮሚቴው አሳስቧል ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ይልማ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በ2020 በአፍሪካ ብቸኛዋ ሳተላይት ያመጠቀች ሀገር መሆኗን ገልጸው ፣ በቋሚ ኮሚቴው በኩል የተነሱ አስተያየቶች ትክክለኛ መሆናቸውንና የተጠቀሱትን ክፍተቶች በቀጣይ ለመፍታት እንደሚሰሩ መናገራቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡