ኢድ አልአድሃ አረፋ በዓልን የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ማሳለፍ ይገባል

ሰኔ 8/2016 (አዲስ ዋልታ) ሕዝበ ሙስሊሙ የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓልን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብና ያለውን በማካፈል መሆን እንዳለበት የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡

ምክር ቤቱ መላውን የእስልምና እምነት ተከታዮች ለ1 ሺሕ 445ኛው ዓመት ሂጅራ የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

ሙስሊሙ ህብረተሰብ በዓሉን ሲያከብር በሃይማኖቱ አስተምህሮ መሰረት የተቸገሩ ወገኖቹን በማሰብና ያለውን በማካፈል እንዲሆን አስገንዝቧል።

የምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ሃጂ ኢብራሂም ቱፋ ህዝበ ሙስሊሙ በዓሉን ሲያከብር በተለያዩ ምክንያቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ የሚገኙ ወገኖችን፣ አቅመ ደካሞችንና አሳዳጊ የሌላቸውን ህጻናት በመደገፍ እንዲያከብር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢድ አልአድሃ አረፋ በዓል ከፆምና ፀሎት ሃይማኖታዊ ሥርዓት በኋላ የሚከናወንና በእስልምና ሃይማኖት ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንደዚሁም ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር አንድነቱንና ወንድማማችነቱን በሚያጠናክር መልክ በዓሉን ማሳለፍ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

በመካሄድ ላይ በሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ህዝበ ሙስሊሙ ንቁ ተሳትፎና ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡