መስከረም 17/2017 (አዲስ ዋልታ) እስራኤል ሃማስን እስክታጠፋ እና ሙሉ ለሙሉ ድል እስክታደርግ ባጋዛ እያካሄደች ያለውን ጦርነት እንደምትቀጥል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢኒያሚን ኔታኒያሁ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተባበሩት መንግስታት 79ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር “ሃማስ መጥፋት አለበት፤ ሀማስ በስልጣን ላይ ከቆዬ፣ እንደገና ተሰባስቦ እስራኤልን እየደጋገመ ያጠቃታል” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራቸው ከሄዝቦላህ እና ከኢራን ጋር ስለገባችበት ግጭትም ንግግር አድርገዋል። “እስራኤል ግቦቿን እስክታሳካ ድረስ ሄዝቦላህን ማዳከሟን ትቀጥላለች” ሲሉ አስረግጠዋል።
እስራኤል ከሊባኖሱ ሄዝቦላህ ጋር የገባችበትን ግጭት እንድታቆም ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበላትን ጥሪ እንደማትቀበል የገለጹት ኔታንያሁ አገራቸው ዛሬ ብቻ ከ25 በላይ ሰዎችን ህይወት የቀጠፈ ጥቃት ሰንዝራለች።
ኢራንን በተመለከተ ሲናገሩ “ለቴህራን አምባገነኖች መልዕክት አለኝ። ጥቃት ከሰነዘራችሁ፣ እኛም በምላሹ አናጠቃለን። በኢራን የእስራኤል ረጅም እጆች የማይደርሱበት ቦታ የለም፤ በመካከለኛው ምስራቅም እንዲሁ” ሲሉ አስፈራርተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባበሩት መንግስታትንም “ጸረ-ሴማዊ” ሲሉ ጠንከር ባሉ ቃላት ወርፈውታል። ተቋሙ እስራኤል በአለም አገራት ዘንድ እንድትገለል በማድረግ “የሞራል መቆሸሽ” እንደገጠመውና “የጸረ-ሴማዊ አረንቋ” ውስጥ ተዘፍቋል ሲሉ ቁጣቸውን ገልጸዋል።
በተሰብሳቢዎቹ ፊት እንዲህ አሉ፣ “እንግራችኋለሁ፣ አይሁዳዊቷ አገር እስራኤል እንደ ሌሎች አገራት እስከምትቆጠር ድረስ፣ የጸረ-ሴማዊ አረንቋው እስኪደርቅ ድረስ፣ የተባበሩት መንግስታት በብዙ አመዛዛኝ ሰዎች ዘንድ የተናቀ አስመሳይ ተደርጎ ይወሰዳል” ማለታቸውን አልጃዜራ ዘግቧል።