እስራኤል በኢራን ላይ የአጸፋ ጥቃት ሰነዘረች

ሚያዝያ 11/2016 (አዲስ ዋልታ) እስራኤል ከኢራን ለተቃጣባት የሚሳኤልና ድሮን ጥቃቶች የአጸፋ እርምጃ መውሰዷ ተገለጸ።

እስራኤል ኢስፋሃን በተባለ የማዕከላዊ አራን አካባቢ ባሉ ወታደራዊ ካምፖች ላይ በድሮኖች ጥቃት መሰንዘሯ ነው የተጠቀሰው።

ይህን ተከትሎ ኢራን የጸረ-ሚሳኤል መከላከያ ማስወንጨፏንና የተተኮሱባትን ሦስት ድሮኖች መታ መጣሏን አስታውቃለች።

ኢስፋሃን የኢራን አየር ኃይል እና የኒዩክሌር ጣቢያ የሚገኙበት ከተማ ሲሆን በአካባቢው የተሰማው ፍንዳታ ኢራን ያስወነጨፈቻቸው የጸረ ሚሳኤል መከላከያ መሆኑን አገሪቱ ባወጣችው መረጃ ገልጻለች።

የእስራኤልን ጥቃት ተከትሎ የአየር በረራዎች ተስተጓጉለው እንደነበርና በአሁኑ ሰዓት በረራ መጀመሩን እንዲሁም አካባቢው ወደ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መመለሱን የአልጃዚራ ዘገባ አመላክቷል።

በፈረንጆቹ ሚያዝያ 1 ቀን እስራኤል ሶሪያ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ላይ ባደረሰችው ጥቃት 13 ዜጎቿ መገደላቸውን ተከትሎ በእስራኤል ላይ ባሳለፍነው ቅዳሜ 300 ሚሳኤልና የድሮን ጥቃት ማድረሷ ይታወሳል።

ለኢራን ጥቃት እስራኤል አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ ዝታ እንደነበርም የሚታወስ ነው።

የሁለቱ አገራት የሰሞኑ ግጭትን ተከትሎ አገራት ዜጎቻቸውን ወደ እስራኤል እንዳይጓዙ እያስጠነቀቁ ነው።

ከስውር ጦርነት አልፎ ወደ ይፋዊና ቀጥተኛ ግጭት ውስጥ የገባው የሁለቱ አገራት የሰሞነኛ ፍጥጫ በቋፍ ላይ የነበረ የአካባቢውን ሰላምና ጸጥታ ወደለየለት ጦርነት እንዳይከተው ተሰግቷል።