እስራኤል እና ፍልስጤም የተኩስ አቁም ስምምነት አደረጉ

ግንቦት 13/2013 (ዋልታ) – በእስራኤል መንግሥት እና በፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሃማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት መደረጉ ተገለፀ፡፡
ተኩስ አቁሙ ከተተገበረ በኋላ በርካታ ፍልስጥኤማዊያን በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ለመግለፅ የወጡ ሲሆን አንድ የሃማስ ባለስልጣን ‹‹አሁንም ጥይታችንን እንዳቀባበልን ነው›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ከመስጊዶች የሚሰሙ የድምፅ ማጉያዎች ‹‹በእየሩሳሌሙ ሰይፍ› ውጊያ ትግላችን ድል አስገኝቷል›› የሚሉ መልክቶችን አስተጋብተዋል።
ሁለቱም አካላት በፍልሚያው አሸናፊነታቸውን አውጀዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የተኩስ አቁሙ ‹‹ለለውጥ ሃቀኛ እድል የሚሰጥ ነው›› ሲሉም ስምምነቱን ገልፀውታል።
ለ11 ቀናት የቆየው ይህ ግጭት እስካሁን የ240 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን አብዛኛው ህልፈት የተመዘገበው በጋዛ መሆኑ ተገልጿል።
በግጭቱ 100 ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ 232 ሰዎች በጋዛ ህይወታቸውን አጥተዋል።
እስራኤል ከዚህ ውስጥ ቢያንስ 150 ያህሉ ተዋጊዎች ናቸው ብላለች።
ሃማስ እስካሁን ድረስ የሞቱ ተዋጊዎቹን ቁጥር ይፋ አላደረገም ተብሏል።
ትላንት ሃሙስ ብቻ እስራኤል 100 የሚጠጉ የአየር ጥቃቶችን በተለይም በሰሜናዊ ጋዛ ያሉ ሃማስ ይጠቀምባቸዋል ባለቻቸው መሰረተ ልማቶች ላይ የፈፀመች ሲሆን ሃማስ በአፀፋው ሮኬት ተኩሷል።
በእስራኤል በተያዙ ምስራቃዊ የኢየሩሳሌም አካባቢዎች ለሳምንታት እየጋለ የሄደው ውጥረት ከ11 ቀናት በፊት ወደ ውጊያ ማደጉ ይታወሳል ሲል ቢቢሲ በዘገባው አስታውቋል ፡፡