እንደወያኔ ከስህተቱ የማይማር ፓርቲ በመጨረሻ መራራውን ፍሬ ያጭዳል – ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ዑመር

በፌደራል ፖሊስ የሚፈለጉ የህውሃት ጁንታ ቡድን አባላት ስም ዝርዝር
እንደወያኔ ጊዜን ወደኋላ የሚወስድ እና ከስህተቱ የማይማር ፓርቲ በመጨረሻም መራራውን ፍሬ እያጨደ ነው ሲሉ የሱማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ ዑመር በአልጀዚራ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ ገልጸዋል፡፡
ህወሓት በ1970ዎቹ ከኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አገዛዝ ነፃ ለመውጣት ከሚታገሉ በርካታ አማፅያን መካከል አብላጫውን ከትግራይ ክልል በተውጣጡ አባላቱ አንዱ ሆኖ ነበር ትግሉን የጀመረው፡፡ በዚያን ጊዜ የትግራይ ማህበረሰብ በቀድሞ ስርዓት በደል ደርሶበታልና ከግንባሩ ጎን ነበር፡፡
በመንገዱም እጅግ የላቀ ብሄረተኝነትን እና የጎሰኝነት አስተሳሰብን ከጥቃት ስሜት ጋር በማቀናጀት በተለይም ፊውዳል ብሎ በሰየመው የአማራ ብሄር ልሂቃን እና ኮሚኒስቶች ላይ ያነጣጠረ ርዕዮተ-ዓለምን አዳበረ፡፡
“እኛ እና እነሱ” የሚለውን ከፋፋይ ሀሳቡን ያሰራጭም ጀመር ሲል ያትታል የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጽሑፍ፡፡ የትግራይ ህዝብ በጠላቶች የተከበበ መሆኑን እና ጠበቃው እና ህልውናውን የሚያረጋግጥለት ህወሃት ብቻ ነው የሚል መርዙን በማህበረሰቡ ዘንድ ማሰራጨቱን ይጠቅሳሉ፡፡
ፓርቲው በፈረንጆቹ 1991 የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) በሚል ጥምረት ውስጥ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ የትግራይ ክልላዊ መንግስት በህወሃት ቁጥጥር ስር ወደቀ፡፡
እንደ ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ እይታ ስልጣኑ ፓርቲው በመላው ኢትዮጵያ እና በትግራይ ህዝብ መካከል ከፋፋይ ርዕዮተ ዓለሙን እንዲያራምድ አስችሎታል፡፡
ህወሓት ዋና አዲስ አበባን መቆጣጠር የቻለበት ሲሆን ከ1983 እስከ 2004 ድረስም በሊቀመንበሩ መለስ ዜናዊ ተመርቷል፡፡
በዚህ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ህዝብ በጋብቻ፣ በንግድ፣ በሃይማኖት እና በባህል ያለውን ትስስር ውህደት የካደ እና የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በእርስ የማይታረቅ ልዩነት ያላቸው ብሄረሰቦችን ያቀፈ ነው የሚል የተሳሳተ ትርክትን ያሰራጭ የነበረው በእርሳቸው የአመራር ዘመን እንደነበርም ጽሑፋቸው ያትታል፡፡
በዚህ የተሳሳተ ትርክት ውስጥ ታዲያ እኩልነትን ያመጣና ለኢትዮጵያ የሰላም ዋስትና እንደሆነ እራሱን ይቆጥር እንደነበር ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ በጽሑፋቸው ገልጸዋል፡፡
የሩዋንዳውን የሁቱና ቱትሲ የዘር ጭፍጨፋ ታሪክ በብሄራዊ መገናኛ ብዙሀን በብዛት እንዲሰራጭ በማድረግ ሰዎች መብታቸውንና ነፃነታቸውን ከጠየቁ መበታተን እድላቸው እንደሚሆን የሚያሳይ ማስፈራሪያውን ያዘንብ እንደነበር ያወሳሉ፡፡
ከመለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ ህወሓት በኢህአዴግ ውስጥ የበላይነቱ አረጋግጦ የነበረ ቢሆንም ከብዙ ዓመታት በኋላ በማህበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ግፊት በፈረንጆቹ 2018 በኢትዮጵያውያን ለውጥ ታየ፡፡
ህወሓትም በአዲስ አበባ የነበረውን ስልጣን አጣ፡፡ ኢህአዴግም ቢሆን ከአንድ ዓመት በኋላ ተበተነ፡፡ የተቀረው የአገሪቱ ክፍል አዲሱን ለውጥ ተቀበለ፣ ሕወሃት ግን የቀድሞውን ከፋፋይ ርዕዮተ-ዓለም አስጠብቆ እንዲያውም ከቀድሞው በበለጠ ማራመዱን ቀጠለበት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በ2019 የፈጠሩት የብልጽግና ፓርቲ ወሳኝ የፖለቲካ እና ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ወደ ፊት ለማራመድ ሲንቀሳቀስ የትህነግ ቡድን ደግሞ በተቃራኒው የትግራይ ህዝብን ሊያጠቃ እንደመጣ የሚያሳይ ትርክቱን ለማህረሰቡ ስለማሰራጨቱ አትተዋል፡፡
በትግራይ ክልል ቴሌቭዥን እና በሌሎችም የመገናኛ ብዙሃን የ1980ዎቹን የሽምቅ ውጊያ የጦርነት ዘጋቢ ፊልሞችን እና ቀረፃዎችን በተከታታይ ያስተላልፍ እንደነበር የሚያወሱት፣ ይህም የትግራይ ህዝብን የከበባ ስሜት እንዲሰማው ማድረግና ለጦርነት ማነሳሳት ዓላማ ያደረገ ነበር ይላሉ፡፡
ህወሓት ስልጣኑን ካጣበት ጊዜ ጀምሮ ለውጡን ለመቀልበስ በሚያስችል ህገወጥ ድርጊቶች ላይ ተሰማርቶ ነበር ሲሉ በጽሑፋቸው የሚገልፁት ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ፣ በትግራይ ክልል ህገወጥ ምርጫ እንዲካሄድ ስለመደረጉም ያነሳሉ፡፡
በመላ ሀገሪቱ ሰላምን የሚያውኩ ወጣቶችን ገንዘብ በመስጠት ያሰማራው ይህ ቡድን በስተመጨረሻም በሰሜን እዝ መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙንም ጽሑፋቸው ያትታል፡፡
ለዚህም ነው የፌዴራል መንግስት በመላው ትግራይ የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲል ወደ ህግ ማስከበር ስራው የገባው ሲሉም እየተከናወነ ያለውን የህግ ማስከበር ተግባር ያስረዳሉ፡፡
የህወሓት ስብስብ ርዕዮተ-ዓለም የትግራይን ህዝብ ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመለያየት ለረጅም ዓመታት የጣረበትና ኢትዮጵያን ለመበታተን የለፋበት የጉዞ ምዕራፍ ይህን ገፅ የተላበሰ ነበር ያሉት ፕሬዝዳንት ሙስጠፌ፣ ነገር ግን አዲሱ የኢትዮጵያ ትውልድ የጎሳ አክራሪነትን እና ግጭትን ውድቅ በማድረግ እድገትን እና ሰላምን ለመቀበል ስለመወሰኑ አንስተዋል፡፡

 

(በትዕግስት ዘላለም)