ከባሕር ዳር – ዳንግላ የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ጥገና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

መጋቢት 13/2014 (ዋልታ) ከባሕር ዳር – ዳንግላ የሚሄደው 66 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ጥገና ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ፡፡

በኤሌክትሪክ አስተላለፊ መስመር ላይ የታወር ብረት ተሰርቆ ምሰሶዎች በመውደቃቸው አገልግሎቱ መቋረጡን አስታውሷል፡፡

በአሁን ወቅት የጥገና ሥራው ተጠናቆ ደንበኞች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘታቸውን የባሕር ዳር ዲስትሪክት ትራንስሚሽን ሰብስቴሽን ኃላፊ ፈለቀ ዳኘው አስታውቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ዲስትሪክት ሠራተኞች አገልግሎቱን ወደ ነበረበት ለመመለስ ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርጉ እንደቆዩና የጥገና ሥራውን በማጠናቀቅ ከተሞቹ ተቋርጦባቸው የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኙ ማድረጋቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በተፈፀመው ስርቆት ምክንያት ከዳንግላ እና ፓዌ ሰብስቴሽኖች ኤሌክትሪክ በሚያገኙ ዳንግላ፣ ዱርቤቴ፣ መራዊ፣ ኮሶበር፣ ግምጃ ቤት፣ ቻግኒና በአካባያቸው ባሉ ከተሞች የኤሌክትሪክ ኃይል ተቋርጦ መቆየቱንም ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW