ከአዲስ አበባ የተወጣጡ የስፖርት ልዑካን ከአምቦ ከተማ ነዋሪዎች ጋር የጋራ የአካል ብቃት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ አደረጉ

መጋቢት 26/2013 (ዋልታ) – “አብሮነታችን ለሀገራችን፣ ለሰላማችን፣ ለአንድነታችንና ለወንድማማችነት” በሚል መሪ ሃሳብ በአምቦ ከተማ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተካሂዷል፡፡

በስፖርታዊ የአካል ብቃት እንቅስቃሴው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነን ጨምሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይ ፣ የአዲስ አበባ ከተማ  ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር በላይ ደጀን፣ የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ናስር ሁሴን ፣የአምቦ ከተማ ከንቲባ አቶ ሳሂሉ ድሪብሳ እና በርካታ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።

በመርሃ ግብሩ አቶ ጥራቱ በየነ  የአዲስ አበባ እና የአምቦን ከተሞች የእህትማማችነት  ግንኙነት በልማት፣ በሰላም ፣በአብሮነት በማገናኘት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የማስ ስፖርት ከነዋሪዎቿ ጋር በመስራታቸው መደሰታቸውን ገልፀዋል።

አብሮነትንና ሰላምን ለማረጋገጥ ከዚህ በፊት ከደብረ ብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጋር ተመሳሳይ የወዳጅነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴ መካሄዱን አስታውሰው በሌሎች ክልል ከተሞችም መሰል ተግባራት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

የአምቦ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሳሂሉ ድሪብሳ በበኩላቸው፣ የሁለቱ እህት ከተሞች የአንድነት፣ የሰላም እና የአብሮነት ግንኙነት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ሰላምን አብሮነትን እና አንድነትን ለመግለፅ በመምጣታቸው በከተማዋ ህዝብ ስም ምስጋና ማቅረባቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።