ከአጠቃላይ የወጭ ምርት 2.4 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል – ሚኒስቴሩ

ሚያዝያ 15 /2013 (ዋልታ) – በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ከአጠቃላይ የወጭ ምርት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ መገኘቱን የንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በወራቶቹ የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት የሚረዱ ተግባራት መከናወናቸውንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።

የሚኒስቴሩ የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም የሚገመግም ጉባኤ ዛሬ በአርባምንጭ ከተማ ተጀምሯል።

በመስሪያ ቤቱ የዕቅድና በጀት ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ አለፈ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ከአጠቃላይ የወጭ ምርት 2 ነጥብ 4 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ተገኝቷል።

ገቢው የተገኘው ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተላኩ የግብርና፣ የማኑፋክቸሪንግና የማዕድን ምርት ሽያጭ መሆኑን ገልጸዋል።

ከግብርና ምርቶች ቡና፣ አበባ፣ የቅባት እህል፣ የእንስሳት ተዋጽኦና ጥራጥሬ፣ ከማኑፋክቸሪንግ ጨርቃጨርቅ፣ አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች እንዲሁም ከማዕድን ምርት ወርቅና ሌሎች የከበሩ ማዕድናት ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን ጠቅሰዋል።

እንደ ኢዜአ ዘገባ ከምርት ጥራትና ህጋዊነት ጋር በተያያዘም በኮንትሮባንድና ከደረጃ በታች የሆኑ ምርቶችን በመቆጣጠር የተሻለ አፈጻጸም መመዝገቡን ጠቁመዋል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍም የሲምንቶ አቅርቦት ችግርን ለመቅረፍ በተወሰደ እርምጃ አዎንታዊ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ዳይሬክተሩ አመልክተዋል።

ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በበኩላቸው የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል።

“በሀገር ውስጥ የሚታየውን የኑሮ ውድነት ለማቃለል ባለሀብቶች መሰረታዊ ሸቀጦችን ከውጭ ሀገራት በቀጥታ እንዲያስገቡ በማድረግ ገበያ ለማረጋጋት ተሰርቷል” ብለዋል።

በተሰሩት ሰራዎች መሰረታዊ የፍጆታ ምርቶችን ህብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት እንዲችል መደረጉን አመልክተዋል።

ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ416 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት፣ ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳር፣ 10 ሚሊዮን ኩንታል ሩዝ፣ ስንዴና የስንዴ ዱቄት ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ መደረጉን ጠቀሰዋል።

በመድረኩ የክልሎች አፈጻጸም የሚገመገም ሲሆን በገበያና ኢንዱስትሪ ዘርፎች የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት አቅጣጫ እንደሚቀመጥም ከመርሀ ግብሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ለሁለት ቀን በሚቆየው የግምገማ መድረክ ከሁሉም ክልሎች የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አካላትና ተጠሪ መስሪያ ቤቶች ተገኝተዋል።
<img class=”j1lvzwm4″ src=”data:;base64, ” width=”18″ height=”18″ />