ከ800 በላይ ጥይቶችን በበቆሎ ውስጥ ደብቆ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ

ሚያዝያ 04/2013 (ዋልታ) – በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ከ800 በላይ ጥይቶችን በበቆሎ ውስጥ ደብቆ ሲያዘዋውር የነበረ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ግለሰቡ ወንጀሉን የፈፀመው በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አውቶቡስ ተራ ትንሿ መናኸሪያ ግቢ ውስጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ግለሰቡ በሁለት ከረጢት በያዘው በቆሎ ውስጥ 200 የብሬን እና 668 የክላሽ ንኮቭ በአጠቃላይ 868 ጥይቶችን ቀላቅሎ በመደበቅ በተሽከርካሪ ጭኖ ለማዘዋወር ሲንቀሳቀስ በወቅቱ በስራ ላይ በነበሩ የመናኸሪያው የስነ-ስርዓት ተቆጣጣሪዎች ጥርጣሬ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
የአውቶቡስ ተራ መናኸሪያ ሥነ ስርዓት ተቆጣጣሪዎች ከዚህ በፊትም በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ የነበሩ ሕገ- ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እና ሌሎች ወንጀሎችን በመቆጣጠርና እጅ ከፍንጅ በመያዝ ውጤታማ ስራ መስራታቸውን ኮሚሽኑ አስታውሷል።
ኮሚሽኑ አያይዞም ይህንን ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ በመጠየቅ ለከተማዋ ሰላም እያበረከቱት ላለው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርቧል፡፡