ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ

ሚያዝያ 05/2013 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከካቢኔ አባላት ጋር በመሆን ከማዘጋጃ እስከ መስቀል አደባባይ እየተሰራ ባለው የመንገድ ዳር የማስዋብ ፕሮጀክት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ።
ለከተማዋ ውበት እና ለእንቅስቃሴ አመቺ የሆኑ የመንገድ አካፋይና ዳርቻን የማስዋብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ምክትል ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
በተለይ ከማዘጋጃ ቤት-የአድዋ 00 ኪሎሜትር ጀምሮ እስከ መስቀል አደባባይ ድረስ እየተሰራ ያለው ፕሮጀክት ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መልኩ እየተሰራ ያለ ሲሆን ለእግረኛ፣ ለሳይክል እና ለሌሎች አገልግሎቶች ምቹ ለማድረግ ደግሞ በመንገዱ አካፋይና ዳርቻ ላይ የችግኝ መትከል መርሐግብር መካሄዱን ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል።
አዲስ አበባን እንደስሟ ውብ እና አበባ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው ስራ በሁሉም የከተማዋ መንገዶችና በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ ይቀጥላል መባሉን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሴክሬታሪ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።