ወጋገን ባንክ ከታክስ በፊት 1.1 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገቡን አስታወቀ

ወጋገን ባንክ በተጠናቀቀው የበጀት አመት ከታክስ በፊት 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ትርፍ ማግኘቱን አስታውቋል።

ባንኩ ይህንን ያስታወቀው ባካሄደው 27ኛ መደበኛ የባለአክሲዮኖች ጉባኤ ላይ ይፋ ባደረገው የኦዲት ሪፖርት ነው፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተፈራ ሞላ ምንም እንኳን በበጀት አመቱ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኢኮኖሚ እንቅስቃሴው ላይ በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት በብድር አከፋፈል እና አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ተከትሎ የብድር ወለድ ምጣኔ ቅናሽ የተደረገ ቢሆንም፣ ባንኩ በ2019/20 የበጀት አመት 1 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢ ከ2018/19 በጀት አመት አፈፃፀም ጋር ሲነፃፀር 47 በመቶ ወይም 324 ብር ሚሊየን ብልጫ እንዳለውም ገልጸዋል።

በባንኩ ደምበኞች የተከፈቱ የቁጠባ ሂሳቦች ብዛትም የ38 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 1 ነጥብ 8 ሚሊየን መድረሱን ምክትል ሰብሳቢው ገልጸዋል።

የወጋገን ባንክ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 43 ተጨማሪ ቅርንጫፎችን በመክፈት በበጀት አመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ብዛት 383 ማድረሱንም ተናግረዋል።

በተመሳሳይ ባንኩ በመላው ሀገሪቱ 2 መቶ 97 የኤቲኤም እና 273 የክፍያ ማስፈጸሚያ ፖስ ማሽኖችን በመትከል እንዲሁም የሞባይል የኢንተርኔት እና የወኪል ባንክ አገልግሎቶችን ከማስፋት አንፃር መልካም አፈፃፀም ማስመዝገቡም ተገልጿል።

ባንኩ ማህበራዊ ሃላፊነቱን ከመወጣት አንፃር በተጠናቀቀው የበጀት አመት በመንግስት የሚካሄዱ የልማት ስራዎችን ለመደገፍ እና የኮሮና በሽታን ለመከላከል የሚደረገውን ሀገር አቀፍ ጥረት ለማገዝ ከ31 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉም ታውቋል።

(በሔለን ታደሰ)