ዓለም ባለፉት 100 አመታት 70 በመቶ የሚሆኑ ረግረጋማ ስፍራዎቿን አጥታለች- ተመድ

አለም ባለፉት 100 አመታት 70 በመቶ የሚሆነውን ረግረጋማ ወይም እርጥበት አዘል ስፍራዎቿን እንዳጣች የተባበሩት መንግስታት ደርጅት (ተመድ) አስታወቀ።

በነገው ዕለት ታስቦ የሚለውን አለም አቀፍ ረግረጋማ ወይንም እርጥበት አዘል ስፍራዎች ቀንን አስመልክቶ ተመድ ባወጣው መረጃ የአለም እርጥበታማ ስፍራዎች መጠን በእጅጉ እየቀነሰ መምጣቱን አስታውቋል።

በዚህም ለጥቅም የሚውለው የንጹህ ውሃ መጠን እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ መቀነሱን በመግለጽ፣ በተለይም ባለፉት 100 አመታት የሰው ልጅ የሚጠቀመው የውሃ መጠን በ6 እጥፍ መጨመሩን ገልጿል።

70 በመቶ የሚሆኑት የአለማችን ረግረጋማ ወይም እርጥበት አዘል ስፍራዎች መጥፋታቸውም ተመላክቷል።

በየአመቱም ይህ ቁጥር አንድ በመቶ እየጨመረ እንደሚሄድ እና እርጥበት አዘል ስፍራዎችን ከሚጎዱ ነገሮች መጠበቅ ካልተቻለ በቂ ውሃ ማግኘት ፈተና ሊሆን እንደሚችል ማስጠንቀቁን ኢዜአ ዘግቧል።