ዛምቢያዊው ፓይለት ‘በመብረቅ’እና ውሽንፍር የተመታውን አውሮፕላን በሰላም አሳረፈ

በውሽንፍርና መብረቅ የተመታው የዛምቢያው አውሮፕላን

ንብረትነቱ ፕሮፍላይት የተሰኘ የግል አየር መንገድ የሆነ ዳሽ 8-300 አውሮፕላን 41 መንገደኞችን አሳፍሮ የቱሪስት ከተማ ከሆነችው ሊቪንግስተን የዛምቢያ መዲና ወደ ሆነችው ሉሳካ በመቃረብ ላይ ሳለ በከባድ ውሽንፍርና መብረቅ መመታቱ ነው የተነገረው።

በ19 ሺህ ጫማ ከፍታ ላይ ሲበር የነበረውና በመብረቅ የተመታው አውሮፕላን አፍንጫው ላይ ጉዳት ቢደርስበትም ፓይለቱ በሰላም መሬት እንዲያርፍ ማድረግ በመቻሉ ብዙዎች በማህበራዊ ሚዲያ እያወደሱት ነው።

የፕሮፍላይት የበበራ ማናጀር የሆኑት ፊል ሊምባ 41 መንገደኞቻቸው በሰላም በመድረሳቸው ደስታቸውን ገልፅዋል።

ዳሽ 8-300 የሆነው ይህ አውሮፕላን በሥሪቱ ምክንያት በመብረቁ አፍንጫው ከመጎዳቱ ባሻገር ምንም ጉዳት እንዳልደረሰበት ማናጀሩ ቢገልፁም አየር መንገዱ ባወጣው መግለጫ ግን አውሮፕላኑ ላይ ጉልህ የሚባል ጉዳት ደርሷል ብሏል።

የአየር መንገዱ መግለጫ እንደሚለው እርግጥም አውሮፕላኑ በከባድ ውሽንፍር ተመትቷል። እርግጠኛ ሆኖ በመብረቅም ተመትቷል ለማለት ግን ምርመራ መደረግ አለበት።
(ምንጭ ቢቢሲ)