የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ለ2014 ጥሪ

የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ

ጳጉሜ 5/2013 (ዋልታ) ኢትዮጵያውያን አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸውንና የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጥሪ አቀረበ።

ጉባኤው የ2014 ዓ.ም አዲሱን ዓመት አስመልክቶ ለሁሉም እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።

ሁሉም አማኞች አዲሱን ዓመት ሲቀበሉ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና በጦርነት የተጎዱትን በማሰብና የሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ሊሆን እንደሚገባም ጉባኤው በሰጠው መግለጫ ጥሪ አቅርቧል።

ይህም በማንኛውም ሃይማኖት የተወደደና የተቀደሰ መልካም ተግባር መሆኑንም ነው ያስታወቀው።

አዲሱ ዓመት በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ ፍጹም ሰላም እና አንድነት የምናይበት ስኬትን የምናስመዘግብበት እንዲሆንም ጉባኤው መልካም ምኞቱን ገልጿል።

በሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች፣ አለመግባባቶች፣ በደሎችና ጉዳቶች በዘላቂነት ተፈትተው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሰላምና በመከባበር መንፈስ የምንኖርበት ሊሆን እንደሚገባም ነው የገለጸው።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን አማኞች ስለ ሀገራቸው ሰላም እና አንድነት እንዲሁም ስለወገኖቻቸው ሁለንተናዊ ደህንነት ፈጣሪያቸውን የሚለምኑበት ሊሆን እንደሚገባም ጉባኤው በመግለጫው አመላክቷል።

በተጨማሪም እንደ ሀገር ያጋጠሙ ፈተናዎችን ለማለፍና መጪው ዘመን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የተሻለ እንዲሆን እያንዳንዳችን እንደምንከተለው ሃይማኖት አስተምህሮና ሥርዓት መሰረት ወደ ፈጣሪ አጥብቆ መፀለይ እንደሚገባ ማሳሰቡን የኢዜአ ዘገባ ያመለክታል።