የሊያና ቴሌ ሄልዝ ቴክኖሎጂ ይፋ ሆነ

 

የካቲት 25/2013 (ዋልታ) – የጤና ሚኒስቴር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህክምና ዘርፉን ማዘመንን ታሳቢ ያደረገ “የሊያና ቴሌ ሄልዝ ቴክኖሎጂ” በዛሬው እለት ይፋ ሆኗል::

የጤና ዘርፉን በማዘመን ጤናማ ዜጋ መፍጠርን መርሁ አድርጎ የተዘጋጀው የሊያና ቴሌ ሔልዝ የአገልግሎት ጥራትን ከፍ በማድረግ ማህበረሰቡን ተደራሽ ያደረገ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል ተብሏል::

ይህ ፕሮጀክት የሀገሪቱን የጤና ዘርፍ ከማሳደግ ባለፈም በአገልግሎት ሰጪና ተገልጋይ መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያዘምን እንደሚሆነም ተገልጿል::

መሰል ‘የቴሌ ሜዲስን’ አገልግሎቶች በአሁኑ ወቅት ከሀገር አልፎ ለአለም ስጋት እና የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ሆኖ የቀጠለው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የህክምና አገልግሎቶች በርቀት ለመከወን የሚያግዝ መሆኑም ተጠቅሷል::

ይሁንና ቴክናሎጂው ለሀገሪቱ የመጀመሪያው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ወደ ህክምና ዘርፉ ለመቀላቀልና ለመዛመድ በርካታ ተግዳሮቶች እንዳጋጠመው ተጠቁሟል::

ቴክኖሎጂውም የማህበረሰቡን እንግልት ከመቀነስ የህክምና እንዲሁም የእውቀት አድማሱን ከማስፋት አኳያ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ባሻገር ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራልም ተብሏል::

ጤናን ማሻሻል በሽታን መቀነስ ያስችላል የተባለለት በሊያና ቴሌ ሔልዝ ቴክኖሎጂን መጠቀም የሚሹ አካላት በ7755 የጥሪ ማእከል ስለ ህክምና መረጃ፣ ቀጠሮ እና መሰል አገልግሎቶችን ማግኘት የሚችሉ መሆኑም ተገልጿል::

በመድረኩም የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ሳህረላ አብዱላሂን ጨምሮ ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል::
(በሄብሮን ዋልታው)