የመንገድ ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት ተደረገ

አቶ ካሳሁን ጎፌ

ሐምሌ 08/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ያዘጋጀው የመንገድ ረቂቅ ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት ተደረገ።

በውይይት መድረኩ የትራንስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ፣ የመንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች፣ አማካሪዎች፣ ቢሮ ኃላፊዎች፣ ዳይሬክተሮችና የመሰረተ ልማት ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።

የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በተደረገው ግምገማ የፖሊሲ ሰነዱ ደረጃውን የጠበቀና በቀጣይ ጊዜያት የመንገድ ሀብትን ለማስተዳደር የሚያስችል እንደሆነ ተረጋግጧል።

ረቂቅ ፖሊሲው የመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራን ይበልጥ በማሳለጥ የዘርፉን አፈፃፀም ያዘምናል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ሲሆን፣ አሁን ያለው የመንገድ ተደራሽነት፣ ምቹነትና ፍጥነት እንዲሁም ደህንነት ችግሮችን ማእከል አድርጎ ተዘጋጅቷል ነው የተባለው፡፡

ብሄራዊ ረቂቅ የመንገድ ፖሊሲ 5 ዋና ዋና የፖሊሲ አንኳር ጉዳዮች እና ዝርዝር የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ይዞ የተዘጋጀ ስለመሆኑም ማብራርያ ተሰጥቶበታል።

የትራንስፖርት ሚኒስቴር የ10 ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድን ለማሳካት የሚያስችሉ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂ ዝግጅቶችን በማጠናቀቅ ላይ መሆኑን ተከትሎ ይህም ፖሊሲ ወደ ሚመለከተው አካል ተልኮ በመጽደቅ ተግባር ላይ እንደሚውል ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ገልፀዋል።

በሀገሪቱ በመሠረተ ልማት ዝርጋታ ትልቅ ሥራ በመስራት ላይ የሚገኘው የመንገዶች ባለስልጣን የሀገሪቱን ሰፊ የመሠረተ ልማት ጥያቄና የወሰን ማስከበር ችግሮች ከክልሎች ጋር በመቀናጀት መስራት እንደሚገባም በፖሊሲው ተቀምጧል።

በውይይቱም ረቂቅ ሰነዱን ሊያዳብር የሚችሉ ሀሳቦች ቀርቦ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ የፖሊሲ ሰነዱን ሊያዳብሩ የሚችሉ ሀሳቦችን በግብዓትነት በመጠቀም በአጭር ጊዜ ውስጥ ትኩረት ተሰጥቶት መካተት የሚገባቸውን በማካተት የፖሊሲ ሰነዱ የመጨረሻውን ይዘት ይዞ እንዲመጣ አቅጣጫ መስጠታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ መለክታል፡፡