የመንገድ ደህንነት የትምህርት ካሪኩለም በይፋ ተጀመረ

ሰኔ 07/2013 (ዋልታ) – በትራንስፖርት ሚኒስቴርና ትምህርት ሚኒስቴር የተዘጋጀው የመንገድ ደህንነት የትምህርት ካሪኩለም በይፋ ተጀምሯል::

ለበርካቶች ህይወት መጥፋትና ለንብረት መውደም ምክንያት በመሆን አስከፊ ጠባሳን እያሳረፈ የሚያልፈውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስ የመንገድ ደህንነት ካሪኩለም ያለው አበርክቶ ላቅ ያለ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ተናግረዋል::

ኢትዮዽያ በትራፊክ አደጋ በሚደርሰው አስከፊ አደጋ ሰለባ ከሆኑ ሀገራት ተርታ መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሯ፣ በአለም አቀፍ ደረጃ የትራፊክ አደጋን በግማሽ ለመቀነስ የሚደረገውን አለም አቀፍ ንቅናቄ መቀለቀሏን ገልጸዋል::

የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ በበኩላቸው፣ የመንገድ ደህንነት ትምህርት ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል እንዲሁም በጎልማሶች ትምህርት ውስጥ እንደሚካተት ገልፀው፣ ሁሉም የሀገሪቱን ክፍሎች የሚያዳርሰው የመንገድ ደህንነት ትምህርት ለህፃናት ተደራሽነትም በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

የመንገድ ደህንነት ትምህርቱም በቀጣይ የትምህርት ዘመን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ይሰጣል ተብሏል::

(በሄብሮን ዋልታው)