የማሊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ የሽግግር አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሆነው ተሰየሙ

ግንቦት 21/2013 (ዋልታ) – የማሊ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በአገሪቱ የተደረገው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታን የሽግግር ጊዜ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሰየመ።
ኮሎኔል ጎይታ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ሁለተኛውን መፈንቅለ መንግሥት አድርገው ሥልጣን ከያዙ ከሁለት ቀናት በኋላ ባለፈው ረቡዕ የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝደንት አድርገው እራሳቸውን ሾመዋል።
በምርጫ ሥልጣን ይዘው የነበሩትን ፕሬዝዳንት ቡባካር ኬይታን ከመንበራቸው ባለፈው ነሐሴ ወር ያስወገዱት ወታደራዊ መሪው፤ የፕሬዝደንትነት ቦታውን እንዲይዙ ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
ከመጀመሪያው መፈንቅለ መንግሥት በኋላ ማሊን ወደ ሲቪል መንግሥት የሚመልሰውን አስተዳደር በጊዜያዊ ፕሬዝዳንትነት እና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሲመሩ የነበሩት ባህ ዳዋ እና ሞክታር ኦኔ በሁለተኛው መፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች ታስረዋል።
ኮሎኔል ጎይታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ፕሬዝዳንቱና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል እንዲታሰሩ አድርገዋል።
ነገር ግን ሁለቱ መሪዎች ከሥልጣናቸው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ ሐሙስ ዕለት ከእስር ተለቀዋል።
አርብ እለት በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ ኮሎኔል ጎይታ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ሆነው የአገሪቱን የሽግግር ሂደት አስከፍጻሜው እንዲመሩ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አመልክቷል።
የባለፈው ዓመት የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ የሽግግሩ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ነበር።
ኮሎኔል ጎይታ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚሾምና ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት በተያዘለት ጊዜ ይካሄዳል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።