የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

ሰኔ 1/2014 (ዋልታ) የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ የሚያዘጋጁት የምስራቅ አፍሪካ የጥበባትና ባህል ፌስቲቫል ‹‹ጥበባትና ባህል ለቀጣናዊ ትስስር›› በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 7 እስከ 12 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ቀጄላ መርዳሳ ኢትዮጵያ ፌስቲቫሉን ማዘጋጀት ስታስብ በመሰረታዊነት የቀጣናውን ሕዝብ እርስ በእርስ እንዲተዋወቅ እና የሕዝቦች መልካም ግንኙነት እንዲጠናከር እድል መፍጠርን ታሳቢ አድርጎ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ፌስቲቫሉ በሌላ መልኩ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ አድርጎ ለማሳየትና የምስራቅ አፍሪካ አገራትን የባህል ግንኙነት ለማጠናከር ትልቅ ሚና አለው ብለዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው ፌስቲቫሉ በአሁኑ ወቅት መካሄዱ በተለይ የባህል ዲፕሎማሲ አካል አድርጎ ከመጠቀም አንፃር ጥሩ እድል እንደሆነ ገልፀው በተለይ አንድ አፍሪካን ለመፍጠር እየተደረጉ ካሉት እንቅስቃሴዎች አንጻር ጥሩ ጅማሮ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አስራ አንድ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ይተሳተፋሉ ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ልዩ ልዩ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ የሰርከስ እና የጎዳና ላይ ትርዒቶች፣ ሲምፖዚየም፣ ባህላዊ የምግብ እና የመጠጥ ዐውደ ርዕይ፣ የፊልም ፌስቲቫል እንዲሁም የሙዚቃ እና የኪነ ጥበብ ሥራዎች እንደሚቀርቡ ከባህል እና ስፖርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡