የሰሜን ሸዋና የደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም አበረታች ሥራዎች እየተሠሩ ናቸው ተባለ

ጥር 18/2014 (ዋልታ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአሸባሪው ሕወሓት ቡድን ጉዳት የደረሰባቸው የሰሜን ሸዋ እና ደቡብ ወሎ አካባቢዎችን መልሶ በማቋቋም አበረታች ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን አስታወቀ፡፡

በአምባሳደር የሺመብራት መርሻ (ዶ/ር) የተመራው የቋሚ ኮሚቴው ቡድን በአካባቢው የመስክ ምልከታ እያደረገ ሲሆን በሸዋሮቢት፣ አጣዬ፣ ከሚሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች በአሸባሪው እና ወራሪው የሕወሓት ቡድን የደረሰውን ጉዳት ተመልክተው በየከተሞቹ ካሉት አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

በሸዋሮቢት ጉዳት ለደረሰባቸው ነዋሪዎች ከመንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች የምግብ እና መሠረታዊ ቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ ቢሆንም ተጎጂዎቹን በዘላቂነት ለማቋቋም ግን የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንደሚጠይቅ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጌታሁን ስዩም ለቋሚ ኮሚቴው አባላት አስረድተዋል።

በተደጋጋሚ የጥቃት ሰለባ የሆነችውን የአጣዬ ከተማ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ የሚያስችል የአመራር ሪፎርም በመደረጉ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ተደጋግፈው እየሠሩ ስለመሆኑ የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ወንደሰን ተገኝ ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልፀዋል።

በከሚሴ አካባቢ የተለያዩ አካላት የተሳተፉበት ውይይት ተደርጎ የአካባቢው ሰላም ወደ ቀድሞ እየተመለሰ መሆኑን ከቋሚ ኮሚቴው አባላት ጋር የተወያዩት የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል።

በአሸባሪዎቹ የሸኔ እና የሕወሓት ቡድኖች የወደሙት የከሚሴ ከተማ ጤና ተቋማት ለአጎራባች አካባቢዎች ጭምር አገልግሎት እየሰጡ የነበረ በመሆኑ ልዩ ትኩረት እንደሚያስፈልጋቸው የከተማዋ አመራሮች ጠይቀዋል።

የፌዴራል እና የአማራ ክልል መንግሥት የኮምቦልቻ ከተማን መልሶ በማቋቋም ረገድ ርብርብ እያደረጉ በመሆኑ ወራሪው ቡድን የአካባቢውን ማኅበረሰብ አንገት ለማስደፋት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ያሉት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አሕመድ የሱፍ ናቸው።

በየአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች የሌላን አካል ድጋፍ ብቻ ከመጠበቅ እርስ በርስ በመረዳዳት የመልሶ ማቋቋም ሥራውን ሊያፋጥኑ እንደሚገባ የቋሚ ኮሚቴው ቡድን መሪ አምባሳደር የሺመብራት (ዶ/ር) ለየአካባቢው አመራሮች በሰጡት ግብረ መልስ ጠቅሰዋል።

በየአካባቢው የተጀመረው የአመራር ሪፎርም በጥናት ላይ ተመሥርቶ እንዲቀጥል የቋሚ ኮሚቴው አባላት ማሳሰባቸውን እና ጉዳት የደረሰባቸውን ለማገዝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚሠሩም መግለጻቸውን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።