የሱዳን ጦር ድንበር አልፎ እንዲገባ ኢትዮጵያ ፈቃድ አልሰጠችም – አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

የሱዳን ጦር ድንበር አልፎ እንዲገባ ኢትዮጵያ ፈቃድ ሰጥታለች እየተባለ የሚሰራጨው መረጃ ፍፁም ሀሰት መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስታወቁ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ኢትዮጵያ እና ሱዳን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ወዳጅነት ጥልቀት ያለው መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት ህግን የማስከበር እርምጃ በትግራይ ክልል በጀመረበት ወቅት ሱዳን ድንበሯን በተጠናከረ ሁኔታ እንድትጠብቅ ኢትዮጵያ እንዳሳሰበች የገለጹት አምባሳደሩ የሆነው ግን በተቃራኒው ነው ብለዋል።

የሱዳን ወታደራዊ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ መሬት መያዙ ሳያንስ ከኢትዮጵያ ግዛት አልወጣም የሚል ንግግር እየተሰማ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ አቋም አሁንም ቢሆን ወደ ቀደመው እና ሁለትዮሽ የድንበር ድርድር መሆኑንም አምባሳደር ዲና አስታውቀዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የኤርትራና ሶማሊያ ወታደሮች እንደገቡ የሚሰራጨው መረጃ ሃሰት መሆኑን የጠቆሙት ቃል አቀባዩ ይህን ሃሰት መረጃ የሚያራግቡ ሃይሎች ህግ ማስከበሩን ቀጣናዊ ችግር ለማድረግ የሚሹ ኃይሎች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።

(በሜሮን መስፍን)