የስዊዝ ቦይን ለአንድ ሳምንት ዘግታ የነበረችው መርከብ መንቀሳቀስ ጀመረች

መጋቢት 20/2013 (ዋልታ) – ስዊዝ ቦይን ለአንድ ሳምንት ዘግታ የነበረችው ግዙፏ ዘ ኤቨር ጊቭን መርከብ መንቀሳቀስ መጀመሯ ተገለፀ።

400 ሜትር የምትረዝመው ግዙፍ እቃ ጫኚ መርከብን ከነበረችበት ሁኔታ 80 በመቶ መልኩ ተስተካክላ መንቀሳቀስ መጀመሯን ነው የስዊዝ ቦይ ባለስልጣናት ያስታወቁት።

ባለስልጣናቱ  መርከቧን ሙሉ በሙሉ ለማንቀሳቀስ በዛሬው ዕለት ተጨማሪ ስራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

ዓለም ላይ ከፍተኛ የንግድ ልውውጥ የሚካሄድበት የስዊዝ ቦይ በኤቨር ጊቭን መርከብ ምክንያት ከተዘጋ አንድ ሳምንት ሆኖታል፡፡

በዚህም በየቀኑ 9 ቢሊየን ዶላር የሚገመት የሸቀጥ ግብይት ላይ መስተጓጎል ሲፈጥር ቆይቷል ብሏል ቢቢሲ በዘገባው።

በዚህ መተላለፊያ በየቀኑ ወደ ምዕራቡ ዓለም 5 ነጥብ 1 ቢሊየን ዶላር ዋጋ ያለው ሸቀጥ የሚንቀሳቀስ ሲሆን ወደ ምስራቁ ደግሞ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር የሚገመት ሀብት ይዘዋወርበታል ተብሏል።

ዘ ኤቨር ጊቭን የተሰኘችው መርከብ የአራት እግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ርዝመት እንዳላትና በዓለም ላይ ግዙፍ ከሚባሉ ኮንቴነር ጫኝ መርኮች መካከል አንዷ መሆኗ ይነገራል፡፡

በሰሜናዊ ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኘውን ወሳኝ የባሕር ላይ መተላለፊያን ዘግታ የምትገኘው የጭነት መርከብ ባለቤት የሆነው ጃፓናዊ በመርከቧ ምክንያት በዓለም የንግድ ልውውጥ ላይ ለተፈጠረው መስተጓጎል ይቅርታ መጠየቁ ተነግሯል።

በከባድ ንፋስ ምክንያት መስመሯን ስታ መተላለፊያውን የዘጋችውን መርከብ ለማንቀሳቀስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ የገለጸው የመርከቧ ባለቤት “ነገር ግን የተቻላቸውን ጥረት በማድረግ” ላይ መሆናቸውን ገልጿል።