የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የኤርትራ ስደተኞችን አገልግሎት ወደሚሰጡት ካምፖች ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን አስታወቀ

መጋቢት 30/2013 (ዋልታ) – በትግራይ ክልል ከተዘጉት የኤርትራ የስደተኛ መጠለያዎች የወጡ ስደተኞችን አገልግሎት ወደሚሰጡ ካምፖች በመመለስ ድጋፍና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን የስደትና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በኢትዮጵያ ለሚገኙ ስደተኞች በቂ ድጋፍ እያደረጉ እንዳልሆነ ገልጿል።

በኢትዮጵያ ከ200 ሺህ በላይ የኤርትራ ስደተኞች እንደሚገኙ ለኢዜአ የገለጹት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ፤ በትግራይ ክልል 49 ሺህ ኤርትራዊያን በስደተኛ መጠለያዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል።

ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በፊት በትግራይ ክልል በሽመልባ የስደተኛ መጠለያ 8 ሺህ 400፣ በህጻጽ 11 ሺህ 800፣ በማይዓይኒና በአዲሀሩሽ የስደተኛ መጠለያዎች በድምሩ 29 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች ይኖሩ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሕግ ማስከበር ዘመቻው በጀመረበት ወቅት በኤርትራ ስደተኛ መጠለያዎች ይሰጠው የነበረው አገልግሎት መቋረጡን አስታውሰው፤ የጸጥታ ስጋት በነበረባቸው ሽመልባና ህጻጽ ካምፖች የነበሩ የኤርትራ ስደተኞች ከመጠለያዎቹ በመውጣት ወደ ተለያዩ አካባቢዎች መሄዳቸውን ጠቅሰዋል።

ከድንበር 50 ኪሎ ሜትር መራቅ ቢኖርበትም የሽመልባ ካምፕ ግን ከኤርትራ ድንበር 20 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኝ በመሆኑ መስፈርቱን አያሟላም ብለዋል።

የህጻጽ የስደተኞች መጠለያ በበረሃ የሚገኝና ለኑሮ አመቺ አለመሆኑንም አመልክተው፤ የስደተኞች መጠለያዎቹ መስፈርቱን ስለማያሟሉ በመንግስት ውሳኔ መዘጋታቸውንና የኤርትራ ስደተኞች በአዲ ሀሩሽና ማይ አይኒ መጠለያዎች አገልሎት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

በዚሁ መሰረት እስከ መጋቢት 27 ቀን 2013 ድረስ ከህጻጽና ሽመልባ መጠለያዎች የወጡ 7 ሺህ 16 ስደተኞች ወደ አዲ ሐሩሽና ማይ አይኒ እንዲመጡ መደረጉን ነው አቶ ተስፋሁን የገለጹት።

ከተዘጉት መጠለያዎች ሌሎች ኤርትራዊያን ወደ ትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች፣ አማራና አፋር ክልሎች እንዲሁም አዲስ አበባ እንደሄዱ ለማወቅ መቻሉንም ገልጸዋል።

ኤጀንሲው ባደረገው ማጣራት የኤርትራ ስደተኛ መሆናቸው የተረጋገጡ ዜጎች በያሉበት ሆነው አስፈላጊው ድጋፍ እየተረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙት የስደተኛ መጠለያዎች የኤርትራ ስደተኞች የምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ አቅርቦቶችን ጨምሮ ድጋፍና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

የኤርትራ ስደተኞች በአራት የስደተኛ ካምፖች ያገኙት የነበረው የአገልግሎት ወደ ሁለት ዝቅ በማለቱ በሁለቱ ካምፖች የሚሰጠውን አገልግሎት አቅም ለመጨመር የሚያስችሉ አማራጭ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከሽመልባና ህጻጽ የወጡ ስደተኞችን አገልግሎት በሚሰጡ ካምፖች የመመለስ ስራው እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

“ከካምፕ ውጪ የመኖር ፍላጎት ያላቸው ስደተኞች ደግሞ በከተማ ለመኖር የሚሰጠውን ፈቃድ ለማግኘት አስፈላጊውን መስፈርት ማሟላት ይጠበቅባቸዋል” ብለዋል።

ስደተኞችን በማጓጓዝ ሂደት የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል የጸጥታ አካላት አስፈላጊውን ጥበቃ እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

መንግስት የኤርትራን ጨምሮ ሌሎች በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ደህንታቸው እንዲጠበቅ፣ የሚያስፈልጋቸው ድጋፍና ማኅበራዊ አገልግሎት እንዲያገኙ ባለው አቅም እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ከተለያዩ ጎረቤት አገራት ለሚመጡ ስደተኞች ተገቢውን ድጋፍ ለማድረግ ከተባበሩት መንግስታት የተለያዩ ተቋማትና መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር እየሰራ እንደሆነም አክለዋል።

ይሁንና ዓለም አቀፍ ተቋማትና አጋር አካላት ለስደተኞች በሚፈለገው መጠን ድጋፍ እያደረጉ እንዳልሆነም ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ከ27 አገራት የመጡ ከ970 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞች አብዛኛውን ድርሻ እንደሚይዙ ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ከደቡብ ሱዳን 324 ሺህ፣ ከኤርትራና ሶማሊያ በተመሳሳይ ከ200 ሺህ በላይ እንዲሁም ከሱዳን የመጡ ከ67 ሺህ በላይ ስደተኞች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።

በኢትዮጵያ ስደተኞች የሚኖሩባቸው 27 የስደተኛ መጠለያዎች የሚገኙ ሲሆን ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ሶማሌ፣ አፋርና ትግራይ ካምፖቹ የሚገኙባቸው ክልሎች ናቸው።