የቋራ-መቅደላ ማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት ምክክር እየተካሄደ ነው

መጋቢት 04/2013 (ዋልታ) – የቋራ-መቅደላ ማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የምክክር ጉባኤ በጎንደር እየተካሄደ ነው።

ጉባኤው ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ ከተወለዱበት ቋራ ጀምሮ ለሀገር መሥዋዕት እስከሆኑበት መቅደላ ድረስ ያሉ ታሪካዊ ቦታዎች የቱሪዝም መሥህብ ለማድረግና ለአካባቢው ወጣት የስራ እድል ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑ ተነግሯል።

የቋራ-መቅደላ ማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የምክክር መድረክ በ2010 ዓ.ም ከተካሄደው የመቅደላ 150 ጉባኤ ቀጣይ ክፍል መሆኑም ተገልጿል።

ንጉሱ ከተወለዱበት እስከ ሞቱበት ድረስ ያለውንና የታሪክ አሻራቸው ያረፉባቸውን 4 ዞኖች ያካልላል የተባለው የኢኮ-ቱሪዝም ፕሮጀክት ከ128 ሚሊየን እስከ 180 ሚሊየን ብር እንደሚያስፈልገው ተጠቁሟል።

ፕሮጀክቱ ስራ ሲጀምር ከ5 ሺህ እስከ 8 ሺህ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ እድል እንሚፈጥርም ነው የተገለጸው።

የቋራ-መቅደላ ማህበረሰብ አቀፍ ኢኮ-ቱሪዝምና አካባቢ ጥበቃ ፕሮጀክት የቱሪስት ቦታዎችን ማበልጸግ፣ የስራ እድል መፍጠርን እና በየአካባቢው አረንጓዴ ልማትን የማልማት ስራ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተገልጿል።

በምክክር ጉባኤው አጼ ቴዎድሮስ ለሃገር አንድነት መሠረት የጣሉ የኢንዱስትሪ አቢዮት ያስጀመሩ ድንቅ መሪ በመሆናቸው አሻራቸው ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል።

መድረኩን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከንጋት አግሮ ኢንተግሬትድ ድቭሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን፣ በአማራ ክልል የሚገኙ 10 ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የታሪክ እና የቱሪዝም ምሁራን እንዲሁም አንጋፋ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስ መቅደላ ላይ የተሰውበት 152ኛ አመት ነገ ሚያዝያ 5/2013 ዓ.ም ነው።

(በምንይሉ ደስይበለው)