የብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ ሁሉንም ሕጋዊ መሠረት የያዘና ሕግን የተከተለ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ

ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ እና ለብልጽግና ፓርቲ አባላት ዛሬ መልእክት አስተላለፉ።

በዚሁ መልእክታቸው የብልጽግና ፓርቲን የመመሥረት ሂደት በምሁራን ሲጠና ቆይቶ በየደረጃው ሁሉም አመራሮች እንደተወያዩበት አስታውቀዋል።

በዚህም መሠረት በትናትናው ዕለት ኦዲፒ እና አዴፓ ባካሔዱት አስቸኳይ ጉባኤ በሙሉ ድምፅ ያጸደቁት ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት ደግሞ የደሕዴን አስቸኳይ ጉባኤ እንደሚያጸድቀው ይጠበቃል ብለዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ምሥረታ ሁሉንም ሕጋዊ መሠረት የያዘ እና ሕግን ተከትሎ የተፈጸመ መሆኑንም ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የገለጹት።

በቀጣይም የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራሙን እያሻሻለ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚወስደውን እቅድ በመንደፍ ከሕዝቡ ጋር የሚወያይበት እና የሚያዳብረው ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የመውሰድ ሕልማችን እውን የምናደርግበት ትክክለኛው መንገድ የተጀመረ መሆኑንም አብስረዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ኃይሎች አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አሐዳዊ ሥርዓትን የሚያመጣ፣ የፌዴራል ሥርዓትን የሚያጠፋ የሚል አሉባልታ ሲናገሩ ይደመጣል ብለዋል።

ይሁንና በፕሮግራሙ ላይ በግልጽ እንዳስቀመጥነው የብልጽግና ፓርቲ ኅብረ ብሔራዊት፣ ፌዴራላዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚያጠናክር እና የሚገነባ እንጅ የማያፈርስ መሆኑን ጠቅላይ ሚንስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

በተመሳሳይ ሌሎች ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ በማምጣት እንዲሞግቱ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ጠቅላይ ሚንስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።