የቱሉሞዬ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የመጀመሪያው ጉድጓድ ቁፋሮ መጠናቀቁ ተገለጸ

መጋቢት 15/2013 (ዋልታ) – በአርሲ ዞን ኢተያ አካባቢ የተጀመረው የቱሉሞዬ የከርሰ ምድር እንፋሎት ኃይል ማመንጫ ግንባታ የመጀመሪያው ጉድጓድ ቁፋሮ መጠናቀቁ ተገለጸ፡፡

ፕሮጀክቱ 150 ሜጋዋት ኃይል ለማግኘት በሁለት ምዕራፎች እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

የፕሮጀክቱ የቴክኒክ ኃላፊ ስጉርጉር ጌሪሰን እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ የምትገኝ ሀገር በመሆኗ የእንፋሎት ኃይል ለማመንጨት የሚያስችል ከፍተኛ እምቅ አቅም አላት፡፡

በቱሉሞዬም እስከ 2 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት የሚያስችል እምቅ የእንፋሎት ኃይል መኖሩንም ነው ኃላፊው የተናገሩት፡፡

በሁለት ምዕራፎች 150 ሜጋዋት ኃይል ለማግኘት 10 የተለያዩ ጉድጓዶች እንደሚቆፈር የገለፁት ኃላፊው፣ ለሥራው የሚያግዙ ሦስት የውሃ ጉድጓዶች ቁፋሮ መጠናቀቁንና አራተኛውም በጅምር ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ሩፋት ማይና በበኩላቸው፣ የመጀመሪያው የኃይል ማመንጫ ጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ቁፋሮ መገባቱን ተናግረዋል፡፡

ወደ መሬት ውስጥ መቆፈር ከሚያስፈልገው 2 ሺህ 500 ሜትር ውስጥ አሁን ላይ 1 ሺህ 14 ሜትር መቆፈሩንም ነው የገለጹት፡፡

ግንባታው በ800 ሚሊየን ዶላር ወጪ የሚከናወን ሲሆን፣ ሁለት ዓመታትን እንደሚወስድ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡