የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

መጋቢት 14/2013 (ዋልታ) – የቱሪዝም ዘርፉን በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማዘመን የሚያስችል ስምምነት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተፈራረሙ፡፡
ስምምነቱ የቱሪዝም ልማት፣ የመረጃ አያያዝና ስርጭት፣ የግብይትና እና የማስተዋወቅ ስራዎችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በማገዝ የቱሪዝምን ተደራሽነት ለማስፋት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡
የኦንላይን ጋላሪና ኤግዚቢሽን ድረ ገፅ ማልማትና ስራ ላይ ማዋል፣ ቱሪዝምን በኢ-ቤተመፅሐፍትና አውቶሜሽን መደገፍ፣ ሰነዶችን በዲጂታል መልኩ ተደራሽ ማድረግ፣ ዘመናዊ የዲጂታል ቱሪዝም የክትትልና ድጋፍ ስርዓት መገንባት፤ ዘመናዊ የሆነ የደንበኛ አገልግሎት ስርዓት በቱሪዝም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች መተግበር የስምምነቱ አካል ነው፡፡
ስምምነቱን የኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብረሃም በላይ እና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰው ፈርመውታል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት ያለው የቱሪዝም ዘርፍን የማዘን ስራዎች በተከታታይ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቱሪዝም ዘርፉን ለማዘመንና ከቱሪዝም የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያስችሉ ስራዎች ላይ እያደረገ ላለው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
የዲጂታል ክፍያ ስርዓት መዘርጋት፣ ቨርቹዋል የጉብኝት ስልቶችን ማስፋፋት፣ የክፍያ ስርዓቶችን ማዘመን፣ ዲጂታል ትርጉምና አስጎብኚ ማዘጋጀት፣ ስማርት የቱሪዝም መዳረሻዎችን መገንባት፣ የቱሪዝም ተቋማትን በቴክኖሎጂ ማዘመን በስምምቱ የተካተቱ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ቅድሚያ ከሰጣቸው ዘርፎች ውስጥ አንዱ የቱሪዝም ዘርፍ መሆኑን ከኢኖቬሽንና ቴክሎጂ ሚኒስትር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡