የትግራይ ህዝብ በህግ ማስከበር ዘመቻው ያሳየውን ቁርጠኝነት ወንጀለኞችን በማጋለጥ ሊደግመው ይገባል!

ጁንታው የህወሃት ቡድን “ነበር” ከመባሉ በፊት ራሱን የትግራይ ህዝብ ዋስትና አድርጎ ከመሳሉም ባሻገር የእኔ መኖር ለትግራይ ህልውና ዋስትና ነው እስከማለት ደርሶም ነበር፡፡

ሃገራዊ ለውጡ በኢትዮጵያ እውን ከሆነ እና ቡድኑም በመቀሌ ከመሸገ በኋላ ባሉት ጊዜያት “እኔ ማለት ትግራይ፣ የትግራይ ህዝብ ማለት ደግሞ እኔ” በሚል ዲስኩር ተጠምዶ ማሳለፉም አይዘነጋም፡፡

ምንም እንኳን ቡድኑ በሚያስተዳድራቸው የተለያዩ የሚዲያ አውታሮች ይህን ሲል ውሎ ቢያድርም እውነታው ግን በሃገሪቱ አድራጊ ፈጣሪ በነበረባቸው 27 አመታት ውስጥ ለክልሉም ሆነ ለትግራይ ህዝብ ምንም አለማድረጉ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እንኳን ያላገኘ ህዝብ ነው የትግራይ ህዝብ፡፡

ቡድኑ 27 ዓመታት ከተንደላቀቀበት እና ግፍ ከሰራበት የስልጣን ማማ እንዲወጣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች የህይወት ዋጋ ከፍለዋል፤ በተለይ ደግሞ የትግራይ ልጆች፡፡

ከራሱ ጥቅም ውጭ ስለ ህዝብና ሃገር ግድ የሌለው ይህ ስግብግብ ጁንታ ተራምዶ የመጣበትን መንገድ እና ውድ ዋጋ ከፍሎ ከዚያ ያደረሰውን ህዝብ ፍጹም ዘንግቶ 27 አመታትን እንደዋዛ አሳልፏል፡፡

ሃገራዊ ለውጡን ለመቀበል ብሎም ለማስቀጠል የሚያስችል አቅም፣ ሞራልና ዝግጁነት ያልነበረው ይህ ቡድን ትግራይን ምሽግ፣ የትግራይ ህዝብን ደግሞ ሽፋን በማድረግ እኩይ ተግባራቱን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

ቡድኑ በሚታወቅበት ፕሮፓጋንዳው “እኔ ማለት ትግራይ፣ የትግራይ ህዝብ ማለት ደግሞ እኔ” የሚል ሃሰተኛ ትርክቱን ለህዝቡ ቢግተውም አስተዋዩ የትግራይ ህዝብን ሊያሳስተው አልተቻለውም፡፡

ከሚሰማው ይልቅ የሚያየውን የሚያምነው አስተዋዩ የትግራይ ህዝብ ጁንታው ለህዝብ ተጠቃሚነት ያደረገው አንድም የሚታይ ነገር እንደሌለ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን፣ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የሃገር መከላከያ ሰራዊት የጁንታውን ታጣቂዎች እየደመሰሰ ወደ ከተሞች ሲዘልቅ በሁሉም የትግራይ ከተሞች ደማቅ አቀባበል በማድረግ አሳይቷል፡፡

ይህ ውሳኔ የትግራይ ህዝብን ሰላም ወዳድነት፣ አስተዋይነት እና ከምንም በላይ ደግሞ ከወንጀለኛ ጎን የማይሰለፍ መሆኑን ከማረጋገጡም በላይ አኩሪ ታሪክ በደማቁ ጽፏል፡፡

ህዝቡ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ያሳየውን ቁርጠኝነት ወንጀለኛው ቡድን የተደበቀበትን በማጋለጥ እና በትግራይ መልሶ ማልማትም መድገም ይጠበቅበታል፡፡

መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ካጠናቀቀ በኋላ ወንጀለኛውን ከማደኑ ስራ ጎን ለጎን ትግራይን መልሶ በማልማት እና የእለት ደራሽ ድጋፍ በማድረስ ስራ ተጠምዶ ይገኛል፡፡

ይህ ጽንፈኛው ቡድን ከተሳካለት ዳግም ኢትዮጵያን የመግዛት፣ ካልሆነ ደግሞ ሃገሪቱን የትርምስ ቀጣና የማድረግ ውስጣዊ መሻቱን ለማሳካት በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ፣ በተለይ ደግሞ ለትግራይ ሁሉን የሆነውን የሰሜን እዝ በጠፍ ጨረቃ ወግቷል፡፡

ከዜጎች ሞትና ትርምስ ማትረፍን እንጂ ራሱ መሞትን የማይፈልገው ይህ ቡድን በመንግስት በኩል በተደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ራሱን በኮንክሪት ምሽጎች በመደበቅ ምንም ግንዛቤ የሌላቸውን እና አጥንታቸው እንኳ ያልጠነከረ ወጣቶችን ማግዷል፡፡

ቡድኑ ራሱ ለፈጸመው የሃገር ክህደት ወታደራዊ እውቀታቸው እና የጦርነት ዝግጁነታቸው እምብዛም የሆኑ ሚሊሻዎችን እና ታጣቂዎችን መማገዱ አልበቃህ ብሎት የተማመነባቸው ምሽጎችና የጦር መሳሪያዎች ከመከላከያ ሰራዊቱ ምት ሊከላከሉት እንዳልቻሉ ሲያውቅ እግር አውጭኝ ብሎ ተበታትኗል፡፡

ከትግራይ ህዝብ ጫንቃ የማይወርደው ይህ ቡድን ከህዝብና ከሃገር የዘረፋቸውን ተሽከርካሪዎች እንኳን ጣጥሎ እግረኛ በመሆን ከሚስኪኑ የትግራይ ህዝብ መንደር ተሸሽጓል፡፡

ቀድሞም ቢሆን በኢትዮጵያ የማይደራደረው የትግራይ ህዝብ የሃገር ክህደትን ጨምሮ በተለያዩ ወንጀሎች የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸው የጁንታው ቡድን አባላትን ከተሸሸጉበት ስርቻ በማውጣትና በማጋለጥ ዳግም ታሪክ መስራቱን ቀጥሎበታል፡፡

ይህም ቢሆን ታዳኞቹ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውለው ሃገርና ህዝብ እፎይ እንዲል፣ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ፣ ሀገሪቷ የጀመረቻቸውን ታላላቅ የልማት ፕሮጄክቶቿን በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ፣ በሙሉ አቅም ማልማት እንዲቻል እና ወንጀለኞችን የማጋለጥ ተግባሩን አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡

በሌላም በኩል “እኔ ከሞትኩ…” እንዲሉ አጥፊው ቡድን በታላላቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት እያደረሰ መሸሹ የሚታወቅ ሲሆን መሰረተ ልማቶቹ ተጠግነው በፍጥነት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ መንግስት ከፍተኛ ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

በመሰረተ ልማቶቹ ውድመት በእጅጉ ተጎጂ የሆነው የክልሉ ህዝብ የወንጀለኛ ቡድኑን ርዝራዦች ከማጋለጥ ጎን ለጎን በትግራይ የመልሶ ማልማት ላይ በንቃት በመሳተፍ እና በመደገፍ በህግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት የሰራውን ገድል መድገም ይኖርበታል፡፡

(በነስረዲን ኑሩ)