የቻይና ጦር ሃይል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መድኃኒትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

ግንቦት 06/2013 (ዋልታ) – የቻይና ጦር ሃይል ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባት መድኃኒትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ።
በድጋፍ ርክክቡ የመከላከያ ሚኒስትር ዶክተር ቀነዓ ያደታን ጨምሮ የመከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ እንዲሁም ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተገኝተዋል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትሩ የቻይና መንግስት ከሀገር መከላከያ ጋር በተለያዩ ዘርፎች ላይ በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፣ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ዙሪያ ባደረገው ስብሰባ ቻይና ከኢትዮጵያ ጎን በመቆም ላሳየችው ቁርጠኝነት አመስግነዋል።
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢያን በበኩላቸው፣ የቻይና የጦር ሀይል ለኢትዮጵያ መከላከያ ያደረገው ድጋፍ በሁለቱ ወዳጅ ሀገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ማሳያ ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ የቻይናና ኢትዮጵያ ወታደራዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና ይህም በሁለቱ ሀገራት አመራሮች የተፈረመው የስትራቴጂክ ግንኙነት አንዱ አካል እንደሆነ መናገራቸውን ከመከላያ ሰራዊት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡