የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ አረፉ

የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ

ሚያዝያ 12/2013 (ዋልታ) – የቻዱ ፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ አማጺያንን የሚዋጉ ወታደሮቻቸውን ለመጎብኘት ወደ ጦር ግንባር በሄዱበት ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት ህይወታቸው ማለፉ ተገለጸ።

ፕሬዝዳንቱ በጦር ግንባር ሳሉ ተመተው መሞታቸውን የአገሪቱ ጦር ሠራዊት አስታውቋል።

ፕሬዝዳንት ዴቢ ለህልፈት የተዳረጉት በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል ከአማጺያን ኃይሎች ጋር ባለፈው ሳምንት ማብቂያ በተደረገ ውጊያ ላይ እንደነበር ሠራዊቱ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ላይ ገልጿል።

የቻድ ጦር ሠራዊት በአሁኑ ጊዜ በዋና ከተማዋ ንጃሚና ላይ ጥቃት የከፈቱትን አማጺ ኃይሎችን እየተዋጋ እንደሚገኝ ተነግሯል።

የፕሬዝዳንት ኢድሪስ ዴቢ ሞት የተነገረው ሰሞኑን ቻድ ውስጥ የተደረገው ምርጫ ላይ የ80 በመቶውን መራጭ ድምጽ በማግኘት ለ6ኛ ጊዜ በፕሬዝዳንትነት ለመቆየት የሚያስችል ጊዜያዊነት ውጤት እንዳገኙ ከተገለጸ በኋላ ነወ።

የፕሬዝዳንቱን ሞት ተከትሎ የቻድ መንግሥትና ፓርላማ የተበተነ ሲሆን፣ ወታደራዊ ምክር ቤት አገሪቱን ለቀጣይ 18 ወራት እንደሚያስተዳድር ተነግሯል።

ኢድሪስ ዴቢ ወደ አገሪቱ የሥልጣን መንበር የመጡት ከዛሬ 21 ዓመት በፊት ነበረ።

ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ሊቢያ ውስጥ መሽገው መንግሥታቸውን ለመጣል ከዋጉት አማጺያን ጋር የሚፋለሙትን ወታደሮቻቸውን ለመጎብኘት ነበር የተጓዙት።

አገሪቱ በቴሌቪዥን ላይ በተነበበው መግለጫ ላይ የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ጄነራል አዜም ቤርማንዶዋ አጉና ፕሬዝዳንት ዴቢ “አስከ መጨረሻ አስትንፋሳቸው ድረስ የአገራቸውን ሉአላዊነት ሲከላለኩ ነበር” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።