የአሜሪካ ኢ-ፍትሓዊ ማዕቀብ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን የሚያበላሽ መሆኑ ተገለጸ

ኅዳር 6/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያና ኤርትራ ላይ የሚደረገው ኢ-ፍትሓዊ ማዕቀብ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ቀጣና ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ የሚያደርጉትን ጥረት የሚያበላሽ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በካናዳ የሚሮሩ ኤርትራዊያን ህብረት እና ኤርትራ – አሜሪካዊያን ምክር ቤት በጋራ በመሆን  በሀገሪቱ በአሜሪካ በኩል የተደረገው ማዕቀብን በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥቷል፡፡

በመግለጫው አሜሪካ በድጋሚ የኤርትራን የልማት እና የሀገር ግንባታ ፕሮጀክቶች ለማደናቀፍ፣ እራሷን የመከላከል እና እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጋፋ ማዕቀብ ማድረጓ ተመላክቷል፡፡

አሜሪካ እያራመደች ያለው ፖሊሲ የአገራትን ሉዓላዊነት የሚንድና ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት የጋራ እርምጃዎችን እንዲወስድ የተሰጠውን ስልጣን የሚጻረር ነው ተብሏል።

“ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግስት መረጋጋት እና አንድነት አፍርሳለች” ስትል አሜሪካ ላደረገችው የስም ማጥፋት ውንጀላ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርጊቱን ጣልቃ ገብነት እንደሆነ መግለጹን ጠቅሶ አውግዞታል፡፡

የኤርትራ ጦር ግዛቱን ለማስጠበቅ መሬቷ ላይ መገኘቱን አስመልክቶ ለዓለም ዐቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ቅሬታ አለማቅረቧን መግለጫው አትቷል፡፡

እንደዚህ ዓይነት ቅሬታ የማቅረብ መብት ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ የምዕራባዊያን አለመሆኑን በመግለጽ ጉዳዩ የኢትዮጵያና የኤርትራ መንግሥታትን ዘላቂ ሰላም ለማደናቀፍ ያለመ ነው ብሏል፡፡

ኤርትራ በኅዳር 2013 ዓ.ም በሕወሓት በርካታ ሚሳኤሎች እየተወነጨፈባት እንደነበር በመግለጽ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀፅ 51 መሰረት ኤርትራ እራሷን የመከላከል መብቷን እየተጠቀመች መሆኑንም መግለጫው አመልክቷል፡፡

ኢ-ፍትሃዊና ተንኮል የተሞላበት ማዕቀብ የኤርትራን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ሰብአዊ ፍላጎቶችን የማሟላት አቅምን እስከሚያሳጣ ድረስ በእጅጉ እንደሚያሳስባት በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ በኤርትራ ላይ የተወሰደውን ኢ-ፍትሃዊ ማዕቀብ በማውገዝ አሜሪካ እንደ ሀገር የኢትዮጵያን ሉዓላዊ መብቶች ከመናድ እንድትቆጠብም ጠይቋል።