የአምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ቡድን መቐለን ጎበኘ

መጋቢት 2/2013 (ዋልታ)– የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑ 40 አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በመቐለ ጉብኝት አድርገዋል።

ቡድኑ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል።

ለአምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶች በትግራይ በመካሄድ ስላለው የመልሶ ግንባታ ስራና የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና በአስተዳደሩ ሌሎች አካላት ማብራሪያ ተስጠቷቸዋል።

በገለጻውም የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባት፣ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋም፣ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት በማዳረስ እንዲሁም የመንግስት አገልግሎቶችን በማስጀመር ረገድ የተከናወኑ ተግባራት እና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በተመለከተ ዝርዝር ገለጻ ተሰጥቷል።

በመንግስት በኩል በክልሉ የሰብዓዊ  ድጋፍ እንዲደረግ አስፈላጊው ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን በማውሳት የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲያደርጉ ጥሪ መቀረቡን ከወጪ ጉዳይ ቃል አቀባይ ጽ/ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።