የአካባቢ ጥበቃ ዲፕሎማሲ ላይ ያተኮረ ውይይት መካሄድ ጀመረ

በርካታ የኢትዮጵያ አምባሳደሮች እና ዲፕሎማቶችን ጨምሮ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተሳተፉበት የአካባቢ ጥበቃ ዲፕሎማሲ (Environmental Diplomacy) ላይ ያተኮረ ውይይት በበይነ መረብ  መካሄድ  ጀምሯል ፡፡

ለአራት ቀናት የሚቆየው አውደ ጥናት በአየር ንብረት ለውጥ ሳይንስ እና በአየር ንብረት ዲፕሎማሲ መሰረታዊ ጉዳዮች ፣ በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፖሊሲ ማዕቀፎችና  በድርድር  እንዲሁም፣ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ  ውሳኔ አሰጣጥ ታሳቢዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል።

ዎርክሾፑን  በንግግር የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን  እንዳሉት አውደ ጥናቱ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ መድረክ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች ላይ  ግንባር ቀደም በመሆን ችግሩ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትኩረት እንዲያገኝ የማይናወጥ ቁርጠኝነት ያላት መሆኑን ያሳያል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ  የሚከሰተውን ተደጋጋሚ ድርቅ ፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እና የአንበጣ ወረራ የችግሩ አመላካች መሆናቸውንም ነው የገለጹት።

በማህበረሰቦች ደረጃ  የአየር ንብረት ተጽኖ  ቅነሳና መላመድ ጣልቃ ገብነት ድጋፍን ለማጎልበት  በአየር ንብረት ላይ ለሚደረግ  ዲፕሎማሲ ተገቢውን ትኩረት መስጠት  አስፈላጊ  ነው ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።

የኢትዮጵያ የውጭ አገልግሎት ማሠልጠኛ ተቋም እና የተባበሩት መንግስታት የሥልጠናና ምርምር ኢንስቲትዩት  ዎርክሾፑን በጋራ ማዘጋጀታቸውን  ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያሳያል።