የአፍሪካ ሕብረት የዲጂታል ቅስቀሳ መርሃ ግብር አዘጋጀ

ግንቦት 09/2013 (ዋልታ) – የአፍሪካ ሕብረት የ2021 የአፍሪካ ቀን አስመልክቶ ለ15 ቀናት የሚቆይ የዲጂታል ቅስቀሳ መርሃ ግብር ማሰናዳቱን አስታወቀ።
እ.አ.አ 1963 የቀድሞ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረትን ምስረታን በማስመልከት የአፍሪካ ቀን በየአመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ግንቦት 17፤ በአውሮፓዊያኑ ደግሞ ግንቦት 25 ይከበራል።
ዘንድሮ የሚከበረውን የአፍሪካ ቀን በማስመልከት “እኔ አፍሪካዊ ነኝ” በሚል መሪ ሀሳብ ለ15 ቀናት የሚቆይ የዲጂታል ቅስቃሳ ሊያካሂድ መሆኑን የአፍሪካ ሕብረት አስታውቋል።
ቅስቀሳው የሕብረቱ የሴት የጾታና ወጣቶች ዳይሬክቶሬት የወጣቶች የስራ ክፍል ከቻይናው የተንቀሳቃሽ ምስሎች ማጋሪያ ቲክቶክና ከፈረንሳዩ የሙዚቃ ቪዲዮ የቴሌቪዥን ቻናል ትሬስ ቲቪ ጋር በመተባበር የሚካሄድ መሆኑን ገልጿል።
የዲጂታል ቅስቀሳው “የምንፈልጋትን አፍሪካ ለመገንባት ባህል ስነ ጥበብና ቅርስ ምሰሶዎች ናቸው” ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የ2021 መሪ ሃሳብ ጋር የተያያዘ ነው።
የስነ ጥበብ፣ ባህልና ቅርስን በዲጂታል አማራጮች በማስተዋወቅ በአፍሪካና በሌሎች አገራት የሚኖሩ የአህጉሪቷ ወጣቶች ያላቸው የተለያዩ ማንነቶች የፈጠራ ችሎታቸውን እንዲያሳዩ ማድረግ የቅስቀሳው ዋንኛ አላማ መሆኑ ታውቋል፡፡
በቅስቀሳው በአፍሪካ የሚገኙ ወጣቶችን በማንቀሳቀስ “እኔ አፍሪካዊ ነኝ” የሚለውን መሪ ሃሳብ ፈጠራን ተጠቅመው ትርጓሜ እንዲሰጡትና ሌሎች ወጣቶች በተመሳሳይ ይሄን እንዲያከናውኑ በማድረግ መነቃቃትን ለመፍጠር ታስቧል።