የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች

ሰኔ 29/2013 (ዋልታ) –  “ጊቤ” በሚል ስያሜ የምትታወቀው የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ አገልግሎት መስጠት ጀመረች፡፡

ኢትዮጵያ “ጊቤ” በተባለችው መርከብ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሌ ላንድ በርበራ ወደብ መደበኛ የጭነት አገልግሎት መስጠት ጀምራለች።

መርከቧ “ገልፍ ኢንዲያ ሰብ ኮንቲነንት” ከሚባለው አካባቢ 11 ሺህ 200 ቶን ስኳርና ሩዝ በመጫን ትናንት በርበራ ወደብ ደርሳለች።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት መርከብ የሆነችው “ጊቤ” ወደ ስፍራው ስትገባ አቀባበል ተደርጎላታል።

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሮባ መገርሳ፣ በሶማሊያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ሰኢድ መሐመድ ጅብሪል እና ሌሎች የሚመለከታቸው የዱባይ ፖርትስ ወርልድ (ዲፒ ወርልድ) የወደብ አስተዳደር ኃላፊዎች በወደቡ ተገኝተው አቀባበል አድርገዋል።

በዚህም የኢትዮጵያ መርከብ በበርበራ ወደብ ከ20 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ድርጅቱ ገልጿል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።