የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሲቪክ ማኅበራት ጋር ሁለተኛ ዙር ውይይት አደረገ

መጋቢት 06/2013 (ዋልታ) – የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለመራጮች ትምህርት ፈቃድ ከተሰጣቸው ሲቪክ ማኅበራት ጋር ሁለተኛ ዙር ውይይት አደረገ፡፡
በመጀመሪያው ዙር የሥነ-ምግባር መመሪያ ቁጥር 4/2012 ላይ የሠፈሩትን መሠረታዊ ደንቦች ከሲቪክ ማኅበራት ኃላፊነት፣ በመራጮች ትምህርት ወቅት መካተት ያለባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች፣ ለሲቪክ ማኅበራት የተዘጋጀ ማስታወሻ፣ ሪፖርት ማድረጊያ ቅጽ እንዲሁም የሥነ-ምግባር ደንቡን የተመለከቱ ጉዳዮች በቦርዱ የሲቪክና የመራጮች ትምህርት ስልጠና መሰጠታቸው አስታውሷል፡፡
አካታች የሆነ የመራጮች ትምህርት አስፈላጊነት፤ ከሥልጠናው የሚጠበቁ ውጤቶች እና ምርጫውን አካታች ለማድረግ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች በሁለተኛው ቀን የውይይት መድረክ ላይ ትኩረት ከተደረገባቸው አጀንዳዎች እንደሆኑ ተገልጿል።
የሥርዓተ-ፆታና የአካል ጉዳተኞች አካታችነት መተግበሪያ ዘዴዎች እንዲሁም ከሥነ-ምግባር መመሪያ አኳያ የሲቪክ ማኅበራት ኃላፊነትን በተመለከተ በቦርዱ የሥርዓተ -ፆታ እና አካታችነት ክፍል ባልደረባ እንደሚቀርብ ተጠቁሟል፡፡
የመራጮች ትምህርት አካታችነት አስመልክቶ ዓለም ዐቀፍ ተሞክሮ ባላቸው ባለሙያ ተጨማሪ ግንዛቤ ማስጨበጫ እንደተሰጠበት የቦርዱ መረጃ ያሳያል፡፡