የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለዕድለኞች ሽልማት ሰጠ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለ”ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” እና “ይቆጥቡ፣ይሸለሙ” ዕጣ ዕድለኞች ሽልማት የመስጠት ሥነስርዓት ተከናወነ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ9ኛው ዙር የ”ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” እና የ”ይቆጥቡ፣ ይሸለሙ”  የሽልማት መርኃግብር ዕጣ ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓም በብሄራዊ ሎተሪ አስተዳደር አዳራሽ መውጣቱ ይታወቃል፡፡

ይህንን ተከትሎ ተከትሎ በአዲስ አበባ ሁለት አፓርትመንቶች፣ ሶስት መለስተኛ የጭነት መኪኖች፣ 15 የቤት አውቶሞቢሎች እና 30 ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪዎች በዛሬው ዕለት ለባለ እድለኞች ደርሰዋል።

በዚህም አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ከሚገኙ የንግድ ባንክ ቅርንጫፎች የተወጣጡ ተሸላሚዎች ሽልማቶቻቸውን ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቢ ሳኖን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግ ብሎም በማህበረሰብ ውስጥ የቁጠባን ባህል ለማዳበር በመላው ሀገሪቱ ቅርንጫፎቹን በማብዛት 1 ሺህ 624 ማድረሱን ገልጸው፣ ባንኩ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጅቡቲ እና ሱዳን ቅርንጫፍ ባንኮችን በመክፈት በአለም አቀፍ ደረጃ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

የቁጠባ ባህልን ለማዳበር የሴቶች የቁጠባ ሂደት፣ የወጣቶች እና ታዳጊዋች ለትምህርት የሚውል እና የጋብቻ ቁጠባን ማመቻቸቱንም ፕሬዝዳንቱ ገልፀዋል።

ላለፋት 10 አመታት በቆየው በዚህ የሽልማት ሂደት ከ8 ሺህ 350 የሚበልጡ ተገልጋዮች ተሸላሚ መሆን እንደቻሉ እና በ2004 ዓ.ም 2 ነጥብ 2 ሚሊየን የነበረው የደንበኛ ቁጥር አሁን ላይ ወደ 26 ሚሊየን ከፍ ማለቱንም ተናግረዋል፡፡

10ኛው ለ”ይመንዝሩ፣ ይሸለሙ” እና “ይቆጥቡ፣ይሸለሙ” መርኃግብር በቀጣይ በይፋ እንደሚጀመርም ለማወቅ ተችሏል።

(በቁምነገር አህመድ)