የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፈጣን የኮቪድ-19 መመርመሪያ ማዕከል ከፈተ

ሚያዝያ 18/2013 (ዋልታ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በፈጣን መመርመሪያ መሣሪያዎች የተደራጀ የኮቪድ-19 የምርመራ ማዕከል በአዲስ አበባ ቦሌ አለምአቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከፈተ፡፡

ይህም የአየር መንገዱ ደንበኞች በረራቸውን ከመጀመራቸው በፊት እንዲመረመሩና እና ውጤታቸውን እንዲያውቁ ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡

አየር መንገዱ ከቻይናው የባዮቴክ ግዙፍ ኩባንያ፣ ከቢጂአይ ዘረመል ጥናት ኩባንያ ቅርንጫፍና ከቢጂአይ ሄልዝ ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ነው የኮቪድ-19 የምርመራ ማዕከሉን የከፈተው፡፡

ማዕከሉን ስራ የማስጀመሪያ ስምምነቱን አስመልክቶ በናይጄሪያ የፊርማ ስነስርአት የተካሄደ መሆኑን ኦልአፍሪካን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡

የኮቪድ-19 ምርመራ ማዕከሉን የተከፈተው በአዲስ አበባ በኩል ለሚጓዙ ተሳፋሪዎች መሆኑን ያመለከተው ዘገባው፤ ማዕከሉ በቀን 1 ሺህ የኮቪድ-19 ምርመራዎች የማካሄድ አቅም እንዳለው ገልጿል፡፡

ውጤት በሶስት ሰዓታት ውስጥ የሚደረስ ሲሆን ለምርመራ እና ውጤት ለመጠበቅ የሚወስደውን ጊዜ በመቀነስ የበረራ ሰአት እንዳይዘገይ የሚያደርግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡