የኢትዮጵያ እና ቱርክ የትብብር ስምምነት በሪፎርሙ ከተከናወኑ የዲፕሎማሲ ገድሎች አንዱና ዋነኛው መሆኑ ተገለጸ

ነሃሴ 14/2013 (ዋልታ) – ኢትዮጵያ እና ቱርክ ሁለንተናዊ ግንኙነታቸውን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መስማማታቸው እና የተለያዩ ስምነቶችን መፈራረማቸው በሪፎርሙ ከተከናወኑ የዲፕሎማሲ ገድሎች አንዱና ዋነኛው መሆኑን በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲና ዓለምአቀፍ ግንኙነት መምህር አቶ እንዳለ ንጉሴ ገለጹ፡፡

ከምዕራባውያን የተቀነባበረ መፈንቅለ መንግሥትና የፋይናንስ አሻጥር በፀና አቋምና ጠንካራ አንድነት አሸናፊ ሆኖ መውጣት እንደሚቻል ከቱርክ ታሪክ መማር እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

አቶ እንዳለ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሪፎርም ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ለዓለም ትልቅ መልዕክት ያስተላለፉና የጂኦ ፖለቲካል ለውጥ ያመጡ አስደናቂ የሚባሉ ስምምነቶች፣ ፕሮጀክቶችና መርሃ ግብሮችን ፈፅማለች፡፡

ከኤርትራ ጋር ሰላም ማውረዷ፤ የታላቁን የህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት በስኬት መፈፀሟ እና አገራዊ ምርጫውን በሰላም ማከናወኗ ለዚህ ሁነኛ ማሳያዎች ሆነው የሚቀርቡ ናቸው፡፡

አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ሁለት አህጉራትን የምታገናኘውንና ጠንካራ ኢኮኖሚ ከገነባችው ቱርክ ጋር ያላትን ሁለንተናዊ ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ለማስቀጠል ከቀናት በፊት የፈፀመችው ስምምነት፤ በሪፎርሙ ከተከናወኑ ትልልቅ የዲፕሎማሲ ገድሎች አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

የጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድን የቱርክ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጸመው ስምምነት እጅግ ወሳኝ በሆነ ወቅት የተፈጸመ እንደመሆኑ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ስለመሆኑ የሚያስረዱት አቶ እንዳለ፤ ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በሉአላዊነትና በነፃነታቸው ላይ ለሚመጣ ድርድር እንደሌላቸው እያስመሰከሩ፣ ምዕራባውያን በአንጻሩ በኢትዮጵያ አቋም ተከፍተው ጫና እያደርጉ በሚገኙበት የተፈፀመ መሆኑም ዘርፈ ብዙ ትርጉም አለው ሲሉ አብራርተዋል።