የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ገለጸ

ጥቅምት 4/2015 (ዋልታ) የኢትዮ-ቻይና ወዳጅነት ይበልጥ እንዲጠናከር ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ገለጸ።

የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ በኢትዮጵያ ከቻይና አምባሳደር ዚሀዎ ዚሁዋን ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በርካታ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፋት፣ የሁለቱን ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማጠናከር እንዲሁም የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማስፋት ዙሪያ መክረዋል።

ምክትል ፕሬዚዳንቱ የኢትዮ-ቻይና ዘመናትን የተሻገረ ወዳጅነት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልፅግና ፓርቲ አበክሮ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

በተለይም ድህነትን በመቅረፍ፣ የአረንጓዴ ልማት ስትራቴጂን በማጠናከር እንዲሁም የወጪ ገቢ ንግድ አማራጮችን ለማስፋት ቻይና ቁልፍ አጋር ሆና እንደምትቀጥል ያላቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ በበርካታ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈችም ቢሆን በተለያዩ መስኮች ስኬቶችን እያስመዘገበች እንደምትገኝ ገልጸው ለዚህ ስኬት መመዝገብ የፓርቲው ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ ጠንካራ የመሪነት ብቃት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቅሰዋል፡፡

ከሁለቱ ሀገራት መንግስታዊ ግንኙነት በተጨማሪ በፓርቲ ደረጃ የብልፅግና ፓርቲ እና የቻይናው ኮሚዩኒስት ፓርቲ ግንኙነት እንዲጠናከር ብልፅግና ከፍተኛ ፍላጎት አለው ማለታቸውን ከብልጽግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዚሀዎ ዚሁዋን በበኩላቸው ኢትዮጵያ የቻይና ጠንካራ ስትራቴጂክ አጋር መሆኗን ጠቅሰው ይህ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲያድግ መንግስታቸው አበክሮ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡
በብልፅግና ፓርቲ መንግስት መሪነት ለተፈፀሙ ስኬቶች በሙሉ ከፍ ያለ እውቅና እንደሚሰጡ በመግለጽም ፓርቲው እጅግ ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ የሪፎርም ሀሳቦች መፍለቂያ እየሆነ መምጣቱ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ብለዋል።