የኢትዮ-ቻይና የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በቻይና ቸንዱ ከተማ ተካሄደ

ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበትን 50ኛ ዓመት በማስመልከት የተዘጋጀ የንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም በቻይና ቸንዱ ከተማ ተካሂዷል፡፡

በቾንቺን ቻይና የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽ/ቤት ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን ባዘጋጀው በዚህ ፎረም ላይ የChina Council for the Promotion of International Trade Sichuan Council (CCPIT) እና የChina Chamber of International Commerce Sichuan Chamber (CCIC) ፕሬዝዳንት እና ምክትል ፕሬዝዳንቶች እንዲሁም በኮንስትራክሽን፣ ፈርኒቸር፣ አውቶሞቢል ፣ የመድሃኒት ማምረቻ መሳሪያዎች፣ ጨርቃጨርቅ እና የእርሻ መሳሪያዎች ምርት ላይ የተሰማሩ 13 ኩባንያዎች ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በቾንቺን ቻይና የኢትዮጵያ ቆንሱል ጄኔራል አቶ አንተነህ ታሪኩ በመክፈቻ ንግግራቸው ፎረሙ እ.ኤ.አ በ2020 ኢትዮጵያና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩበት 50ኛ ዓመትን በማስመልከት ከተካሄዱ መርሃ ግብሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን ገልጸው፣ ግማሽ ምዕተ ዓመት ያስቆጠረው ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሁለቱን አገራትና ህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነትና ዘላቂ ልማት ግብ በማሳካት ሂደት ላይ የሚገኝ በመሆኑ ምሳሌያዊና ውጤታማ ነው ብለዋል፡፡

(ምንጭ ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽ/ቤት)