የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት የጋራ ፎረም ሊቋቋም መሆኑ ተገለፀ

የካቲት 12/ 2013 (ዋልታ) – በመዲናዋ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል የጋራ ፎረም ሊቋቋም መሆኑ ተጠቆመ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኤሌክትሪክ ሀይል አገልግሎት በአገልግሎቱ ላይ በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ ከየክፍለከተሞች ስራ አስፈፃሚዎች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።

በመድረኩ በቀረበ ሰነድ ላይም የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ፣ የሃይል አቅርቦት ማነስ እና መብዛትና ሌሎችም ችግሮች በአገልግሎት አሠጣጡ ላይ እንቅፋት መሆናቸው ተገለፀ።

በመዲናዋ በተለይ ምክንያታዊ ያልሆነ የሀይል መቆራረጥ እንደሚገጥምም ተብራርቷል።

ለአገልግሎት መቆራረጥና ሌሌችም ለሚነሱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት ደግሞ በየወረዳው ከሚገኙ ዲስትሪክቶች ጋር ተቀናጅቶ የመስራት ችግር መኖሩም ታውቋል።

የሚቋቋመው የጋራ ፎረምም በኤሌክትሪክ አገልግሎት ላይ የተነሱ ችግሮችን በተቀናጀ መልኩ ለመፍታት እንደሚያስችል በመድረኩ ተጠቁሟል።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ፅህፈት ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመድረኩ ተገኝተዋል፡፡
(በትዕግስት ዘላለም)